ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ-የቻይና የቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

ግንቦት 19/2011 በፋርማሲዪቲካል ዘርፍ ያተኮረው የኢትዮጵያና የቻይና የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሄደ።

ከቻይና ሃናን ግዛት የመጡ የተለያዩ ኩባንያዎች በመድኃኒት ማምረት ተግባር በኢትዮጵያ ስላለው እድል ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም አንድታገኝ ለውጭ ባለኃብቶች ክፍት አድርጋለች።

 በተለይም የአገር ውስጥ ባለኃብቶች በዘርፉ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲሳተፉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ  እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በተለይም ከአራት አመት በፊት የወጣው የዘርፉ የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ ኢንቨስትመንቱን እንዲያፋጥን መቀረጹን አስታውሰዋል።

ያም ሆኖ ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንሰ ወጪ ስለሚጠይቅ እንደሌሎቹ ዘርፎች ያን ያክል እድገት እንዳልታየበት ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በአነስተኛ ቁጥር የፋርማሲዩቲካል ዘርፉን ለመደገፍ የሚያስችል የኢንደስትሪ ፓርክ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት የተካሄደው የኢትዮቻይና የፋርማሲዪቲካል የቢዝነስ ፎረምም ይህንን አገራዊ ጥረት በማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሃናን ግዛት የቻይና አፍሪካ የቢዝነስ ፎረም ማኅበር ፕሬዚዳንት ዊሊያም ዮንግም በኢትዮጵያ በዘርፉ ከፍተኛ አቅም መኖሩን ተመልክቻለው ብለዋል።  

በቀጣይም በዘርፉ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።  በፎረሙ ከ20 በላይ የዘርፉ የቻይና ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም