ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃና የስነ ንጽህናን ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

ግንቦት 19/2011 የንጹህ መጠጥ ውሃና የስነ ንጽህና ችግርን ለመፍታት የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ብድር በማቅረብ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

በሃገር አቀፍ ደረጃ የስነ ንጽህና ሽፋን ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ተመልክቷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ይመር ሃብቴ የፋይናስ ተቋማት ድጋፍ ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ለመምከር በባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለፁት የንፁህ መጥጥ ውሃ አቅርቦትና የስነ ንፅህና ጉድለት የክልሉ አንዱ ቁልፍ ችግር ነው፡፡

በገንዘብ እጥረት ምክንያት የክልሉ መንግስት የንጹህ መጠጥ ውሃና ስነንጽህናን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የደብረ ታቦር፣ የደሴና ሌሎች ከተሞችን ጨምሮ በርካታ የዲዛይን ሥራ የተሰራላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም መንግስት ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ ተግባር መግባት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት በገጠርም ሆነ በከተማ የህዝቡን ስነ ንጽህናን በማሻሻል በኩል ሰፊ ክፍታት መኖሩን ነው አቶ ይመር የገለጹት።

“በመሆኑም ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በዚህ ዘርፍ በመሳተፍና ሰፊ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት  ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ሊያግዙ ይገባል” ብለዋል፡፡

በተለይም በራሳቸው አቅም መስራት ለሚችሉና ተደራጅተው የመስራት ፍላጎት ላላቸው ቡድኖች ብድሩን በመስጠት የመንግስትን የአቅም ክፍተት ሊሞሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

“ በክልሉ የመፀዳጃ ቤት ሽፋን 60 ከመቶ ደርሷል፤ ከዚህ ውስጥ የተሻሻሉ ናቸው ተብለው የሚጠበቁት ከ30 በመቶ አይበልጡም” ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ የሃይጅንና ሳንቴሽን ባለሙያ አቶ አስራት ቢተው ናቸው፡፡

ባለሙያው እንዳሉት የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን ህብረተሰቡ ቢገነባም በግንዛቤ ክፍተት ምክንያት አሁንም የመጠቀም ባህሉ ያደገ አይደለም።

የተገነቡትም ዘለቄታዊነት የሌላቸው መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ የብድር አቅረቦት ከተመቻቸለት ደረጃቸውን የጠበቁና የተሻሻሉ መጸዳጃ ቤቶችን መገንባት እንደሚችል ገልጸዋል።

በዚህም ከስነ ንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዞ እየተከሰተ ያለውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ አስታውቃል፡፡

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም የገጠር ደንበኛ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሙጨ ያለው በበኩላቸው ተቋሙ የህብረተሰቡን የገንዘብ እጥረት የሚቀርፉ በርካታ የብድር አማራጮችን መዘርጋቱን  ገልጸዋል።

ተቋሙ ባለፉት ጊዜያት ለቤት መስሪያ ብቻ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማሰራጨቱን ጠቅሰው፣ ለውሃና ሽንት ቤት ግንባታም ብድር የሚሰጥበት አሰራር እንዳለው ጠቁመዋል።

“ተቋሙ በእነዚህ ዘርፎች ብድር የመስጠት ፍላጎትና የተዘረጋ አሰራር ቢኖረውም በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ብድሩን የሚጠይቅና የሚወስድ የለም” ብለዋል።

በመሆኑም በእዚህ ዘርፍ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራትና የግንዛቤ ችግሩን በመፍታት ህብረተሰቡ የብድሩ ተጠቃሚ እንዲሆን እስከ ቀበሌ ተወርዶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የወተር ዶት ኦርግ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሳልፊሶ ኪታቦ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት መንግስታት በስነ ንፅህና ዘርፍ ስትሰራ የቆየች ቢሆንም ሽፋኑ ከ10 በመቶ አይበልጥም” ብለዋል፡፡

በእዚህም በዘላቂ የልማት ግቦች በ2030 ህዝቡ ሙሉ በሙሉ የራሱ መፀዳጃ ቤት እንዲኖረው ለማድረግ ሃገሪቱ የገባቸውን የቃል ኪዳን ስምምነት ለማሳካት እንደማይቻል አመልክተዋል።

ከድህነት ወላል በታች ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመደገፍ፤ ተበድሮ የመክፈል አቅም ያለውን ህብረተሰብ ደግሞ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ድርጅቱ በዚህ ዓመት ብቻ በአማራ፣ በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች በሙከራ ደረጃ ለሰራው ሥራ 39 ሺህ ሰዎችን ከፋይናስ ተቋት ጋር በማገናኘት 31 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚ  ማድረጉንም አስረድተዋል።

“በቀጣይም ይህን ተሞክሮ በማስፋትና በፖሊሲ እንዲደገፍ በማድረግ የዘላቂ ልማት ግቡ በተወሰነ ደረጃ እንዲሳካ ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እንዲደግፉ መንግስት አቅጣጫ ሊሰጥ ይገባል፡፡” ብለዋል።

በውየይት መድረኩ ላይ  የክልል፣ የዞንና የወረዳ የውሃ፣ የፋይናንስ፣ የጤና ተቃማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም