ለአፍሪካ ልማትና ሰላም በሚካሄዱ ትግሎች የኢትዮጵያ ቁርጠኝነት ቀጣይ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ልማትና ሰላም በሚካሄዱ ትግሎች የኢትዮጵያ ቁርጠኝነት ቀጣይ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ልማትና ሰላም በሚካሄዱ ትግሎች ውስጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አስታወቁ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር "የአፍሪካን ቀን" ዛሬ በተቋሙ አክብሯል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተመስርቶ አህጉሪቱን ወደ አንድነት ያመጣበት እኤአ ግንቦት 25 ቀን 1963 በየዓመቱ "የአፍሪካ ቀን" በሚል በድምቀት ይከበራል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርም በዓሉን አስመልክቶ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን አዋጅን በተመለከተ ለውጪ ጉዳይ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ለማስተዋወቅ የፓናል ውይይት አካሄዷል።
በበዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ፣ የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር አምባሳደር ኳሲ ኳርቴ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎቸ ተገኝተዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ አንስቶ ታሪካዊ ሃላፊነት የተወጣች ከመሆኗ በላይ የአፍሪካ አገራት የሰጧትን ሃላፊነት በፍፁም ታማኝነት እየተወጣችም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን የጠቆሙት አቶ ገዱ የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥና በዲፕሎማሲው ዘርፍም በብቃት ለመወጣት በርካታ የሪፎርም ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ እንዲሆን፣ አህጉራዊ ትስስር እንዲጎለብት፣የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ስምምነት እንዲተገበር እና የአፍሪካ ዜጎች የመዳረሻ ቪዛ እንዲያገኙ እየሰራች ያለችው ስራም ለሃጉራዊ ትስስሩ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ልማትና ሰላም በሚካሄዱ ትግሎች ወስጥ በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ነው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
የአፍሪካ ህብረት ምክትል ኮሚሽነር አምባሳደር ኳሲ ኳርቴ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአህጉራዊውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ከምታደርገው ጥረት በተጨማሪ በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አማካኝነት ለአህጉሩና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ አያበረከተች መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ነፃ የሆነች አገር መሆኗን እና ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ነፃ እንዲወጡ ያነሳሳች አገር መሆኗን የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የአፍሪካ አገራት መቀመጫ ሆና እያገለገለች ያለች እንግዳ ተቀባይ አገር መሆኗንም አውስተዋል።
የአፍሪካ ቀን ከ56 ዓመታት በፊት የነበሩት መሪዎች አፍሪካ ነፃ እንድትወጣ የከፈሉትን መስዋትነት እውቅና የሚሰጥ እና በቀጣይም በዓለም ላይ ታላቋን አፍሪካ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያግዛልም ብለዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአውሮፓውያኑ ግንቦት 25 ቀን 1963 ነበር የተመሰረተው።
የአፍሪካ ሀገራትም ይህ የሚታወስበትን የአፍሪካ ቀን በተለያዩ ሁነቶች ሲያከብሩ ቆይተዋል።
"የአፍሪካ ቀን" የአፍሪካን መራራ የነፃነት ትግል እና ብሩህ ተስፋ በማሰብ የሚከበር በአል ሲሆን፤ አፍሪካውያን ባህላቸውን፣ ትውፊታቸውን እና ስልጣኔያቸውን ለመላው ዓለም የሚያስተዋውቁበት በአል ሆኖ እንደሚከበርም ይታወቃል።