ማልማት የሚፈልጉት ሊሙ የተሰኘው ምርጥ የበቆሎ ዘር ማግኘት እንዳልቻሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ማልማት የሚፈልጉት ሊሙ የተሰኘው ምርጥ የበቆሎ ዘር ማግኘት እንዳልቻሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ
ባህር ዳር ግንቦት 30/2010 በተያዘው የመኽር ወቅት በምርታማነቱ የሚያውቁት ሊሙ የተሰኘው ምርት የበቆሎ ዘር ማልማት ቢፈልጉም ማግኘት እንዳልቻሉ በምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ባለፈው ዓመት ተባዝቶ የተሰበሰበ አምስት ሺህ 600 ኩንታል ሊሙ የበቆሎ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ገልጿል፡፡ አርሶ አደር ኑሬ መንግስቴ በዞኑ ደንበጫ ወረዳ የእግዚሔር አብ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ አሁን በአካባቢው መጣል የጀመረው ዝናብ ለእርሻና ለዘር ስራ አመቺ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል። ቀደም ሲል ካላቸው ተሞክሮ ፈጥኖ በመድረስ በሄክታር እስከ 90 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ የሚያውቁት ሊሙ የተሰኘው ምርጥ የበቆሎ ዘር ዘንድሮ ማግኘት እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት 660 እና 661 የተባሉት የበቆሎ ዝርያዎችን ሳይፈልጉ ወስደው ለመዝራት መገደዳቸውን ጠቅሰው እነዚህ ዝርያዎች በምርታማነታቸው ከሊሙ ዘር በሄክታር እስከ 20 ኩንታል ምርት ዝቅ ያሉ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ በጃቢ ጠህናን ወረዳ የጎርፍ ቃውንችን ቀበሌ አርሶ አደር ተፈራ መለሰ በበኩላቸው በዘር አቅርቦት እጥረት ምክንያት ምርታማ የሆነውን የበቆሎ ዘር ዘንድሮ ባለመዝራታቸው ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል፡፡ በሌላ የበቆሎ ዘር እየሸፈኑት ያለውን ሁለት ሄክታር ተኩል የእርሻ ማሳ ሊሙ በተሰኘው ምርጥ የበቆሎ ዘር ማልማት ቢችሉ ከ200 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት ይጠቀሙ እንደነበር ጠቁመዋል። የእርሻ ማሳቸውን በሌላ የበቆሎ ዘር በመሸፈናቸውም ምርታማነታቸው እንደሚቀንስባቸው ነው የተናገሩት። ሊሙ ከምርታማነቱ በተጨማሪ በ90 ቀናት ውስጥ ፈጥኖ ስለሚደርስ ሰብሉን አንስቶ መሬቱን በሽንብራ ሰብል ዳግም በማልማት ተጨማሪ ምርትና ጥቅም እንዲያገኙ ያስችላቸው እንደነበርም ካለፈው ተሞክሯቸው በመነሳት አውስተዋል። ባለፉት ሶስት ዓመታት የሊሙን የበቆሎ ዘር ተጠቅመው በማልማት የተሻለ ምርት በማግኘት ተጠቃሚ እንደነበሩ በማስተወስ የተናገሩት ደግሞ በወንበርማ ወረዳ የማርወለድ ቀበሌ አርሶ አደር ቸኮል ሁሉቃ ናቸው። ዘንድሮ ባላወቁት ምክንያት ሊቀርብ ባለመቻሉ ከዚህ በፊት የነበረ ሌላ ዘር እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ግድ ሆኖባቸዋል። በተጨማሪም የዩሪያ ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ችግር ዘንድሮም እየተስተዋለ በመሆኑ ያለፈው ዓመት ችግር እንዳይደገም በሚመለከተው በኩል ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ አመልክተዋል። በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሰውመሆን ተገኘ እንዳሉት የበቆሎ ገዳይ በሽታ ከመከሰቱ ጋር ተያይዞ ሊሙ የበቆሎ ዘር የሚመጣው ከሌላ አካባቢ በመሆኑ ዘሩን ማቅረብ አልተቻለም። አነስተኛ ቢሆንም ባለፈው ዓመት በዞኑ ተባዝቶ የተሰበሰበ አምስት ሺህ 600 ኩንታል ሊሙ የበቆሎ ዘር ቀደም ሲል ቀርቦ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን ገልጸዋል። ቡድን መሪው እንዳሉት ባለፉት አራት ዓመታት የሊሙ ዘር በቆሎ አብቃይ በሆኑ ወረዳዎች ተሞክሮ ፈጥኖ በመድረስ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችል የበቆሎ ዝርያ መሆኑ በባለሙያዎችና በአርሶ አደሩ ዘንድ ተመስክሮለታል። ለምርት ዘመኑ አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ማዳበሪያ ከውጭ ወደዞኑ ለማስገባት ታቅዶ እስካሁን ከ900 ሺህ ኩንታል በላይ ተጓጉዞ ለየህብረት ስራ ማህበራት መድረሱን ቡድን መሪው አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥም በጨረታ ችግር ምክንያት ዘግይቶ ከተገዛው ዩሪያ ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ወደዞኑ ተጓጉዞ መቅረብ የቻለው 258 ሺህ ኩንታል በመሆኑ የአቅርቦት እጥረት እንዲከሰት አድርጓል። ማዳበሪያው ወደብ ላይ ቢደርስም በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ፈጥኖ ባለመቅረቡ ዕጥረት ማጋጠሙን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት መምሪያው ከክልሉ ግብርና ቢሮውና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በምርት ዘመኑ በዞኑ ለማልማት ከታቀደው 550 ሺህ ሄክታር መሬት እስካሁን ከ96 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው በበቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ድንችና ሌሎች ቀድሞ በሚዛራ ሰብል መሸፈኑም ታውቋል።