ወቅቱን የጠበቀና የተሟላ የአየር ትንበያ ማግኘት እንዲቻል ኢጋድ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ወቅቱን የጠበቀና የተሟላ የአየር ትንበያ ማግኘት እንዲቻል ኢጋድ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል
ግንቦት 19/2011 የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ወቅቱን የጠበቀና የተሟላ የአየር ትንበያ ማግኘት እንዲችል በትብብር እንደሚሰራ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ገለጸ።
ከመጪው ሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ሶስት ወራት በቀጠናው በሚኖረው የአየር ትንበያና ትንተና ላይ የሚያተኩረው 52ኛው የአየር ትንበያና ትንተና ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በኢጋድ የአየር ትንበያና ምልከታ ማዕከል (ICPAC) ዳይሬክተር ዶክተር ጉሌድ አርታን እንዳሉት፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወቅታዊ የአየር ትንበያ መቅረብ ይኖርበታል።
በመሆኑም ተመራማሪዎች እንዲሁም በአየር ንብረት ትንበያ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ወቅታዊና የተሟላ ትንበያና ትንተና እንዲያቀርቡ ኢጋድ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጠናው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ውሃ፣ የአደጋ ስጋት አመራርና፣ ግብርና፣ ጤናና ኢነርጂ ካሉ ቁልፍ ዘርፎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው መንግስት ዘመናዊና ቀልጣፋ የሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በአጭር ጊዜ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችሉ የሳተላይት ምስሎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ብለዋል።
መረጃ ማዕከላትን ዘመናዊ ማድረግ ከራዳር ጀምሮ እስከ አውቶሜቲክ ዌዘር ስቴሽን የምንላቸው ዳታን በየ 15 ደቂቃው በቀላሉ ማስተላለፍ የሚችል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለምሳሌ ሪሞት ሴንሲንግና የሳተላይት ምስሎችን በመውሰድ የሚመጣውን ዝናብ በአጭር ጊዜ ፕሪዲክት የማድረግ ወይም የመተንበይ ስራዎች እየሰራን እንገኛለን የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ከዚህ ላይ ፎከስ እያደረገ ይሰራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሜቲዎሮሎጂመረጃዎችን ከስነ ውሃ (ሃይድሮሎጂ) ጋር በማገናኘት የወንዞች የውሃ መጠንን በትክክል ለመተንበይ በስፋት እየሰራን ነው ብለዋል።
ከዚህ በመነሳት መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት ሰጥቶ የወንዝ ዳርቻዎችን አረንጓዴ ለማድረግና ጽዱ ከተሞችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል ሚኒስትሩ።
ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ ትንበያና ትንተና ለማግኘትም ከዓለም አቀፍ የሜቲዎሮሎጂ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።