የቀድሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኃላፊዎች በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንደሌላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኃላፊዎች በቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ እንደሌላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 የቀድሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ኃላፊዎች የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሰረተባቸው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ መቃወሚያ እንደሌላቸው አስታወቁ።
በእነ አቶ ኃይለሥላሴ ቢሆን መዝገብ ክስ የቀረበባቸው አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን ፣ አቶ የማነብርሃን ታደሰ ፣ አቶ ሙከሚል አብደላ ፣ ኢንጂነር አሸናፊ ሁሴን /ያልተያዙ/፣ አቶ ያሬድ ይገዙ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሞግሪያ/ያልተያዙ/ እና አቶ ያለው ሞላ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
እነዚሁ ተከሳሾች የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘትና ጥቅሙን ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም የመንግሥት ግዥ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 ድንጋጌንና የማስፈጸሚያ መመሪያውን አንቀጽ 25 እንዲሁም የኤጀንሲውን የግዥ መመሪያ አንቀጽ 10/3 በመተላለፍ ፣ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸሙ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
አዋጁንና መመሪያዎቹን በመተላለፍ ለመከላከያ ሚኒስቴር የመድኃኒት ግዥ ለመፈጸም በኤጀንሲውና በአገር መከላከያ ሚኒስቴር መካከል በተደረገ የዱቤ ሽያጭ ውል መሠረት ግዥው እንዲከናወን ሲደረግ ፣ ግልጽ ጨረታ በማውጣት ግዥ መፈጸም ቢኖርባቸውም ያንን አለማድረጋቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
የቀድሞ የድርጅቱ የግዥ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሙከሚል አብደላ በሕጉ መሠረት የሚፈጸም ግዥ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እያለባቸው ፣ በቀጥታ ሲትረክ ኢንተርናሽናል ከሚባል አቅራቢ ድርጅት ግዥ እንዲፈጸም ሲጠየቁ፣ ግዥው ያለ ውድድር እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ሌሎቹም ተከሳሾች የግዥ አፅዳቂ ኮሚቴ ሆነው በመሰየማቸው በአዋጁና በመመሪያው መሠረት ግዥው መፈጸሙን የማረጋገጥ ኃላፊነት እያለባቸው ፣ሕጉን ያልተከተለ መሆኑን እያወቁ አቅራቢው ድርጅት ያለ ውድድር ቀጥታ ባቀረበው ዋጋ እንዲገዛ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረባቸውን አቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ያለ ውድድር እንዲገዛ ቢደረግ እንኳን፣ የመንግሥትን ጥቅም በሚያስጠብቅ ድርድር እንዲደረግ በመወሰን፣ ወይም የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እያለባቸው አለማድረጋቸውንም አክሏል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ሕግን ባልተከተለ ሁኔታ የ13ሚሊዮን 449 ሺህ 11 ብር ግዥ እንዲፈጸም በማድረጋቸው፣ በዋናነት ወንጀል አድራጊነት እና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተመሥርቶባቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ሕግ በመሰረተው ክስ ላይ ተከሳሾቹ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ ነበር።
ነገር ግን ተከሳሾቹ በተመሰረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ የሌላቸው መሆኑን በመግለጻቸው በስነ ስርአት ሕጉ 130 እና 131 መሰረት የእምነት ክሕደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል።
በሰጡት የእምነት ክሕደት ቃልም በወቅቱ ወይም ስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ሕግና ደንብን ተከትለው መስራታቸውንና ወንጀሉንም እንዳልፈፀሙ ነው ለችሎቱ የተናገሩት።
አቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ክደው የተከራከሩ በመሆኑ አለኝ የሚላቸው ምስክሮችና ማስረጃዎች ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ ተከሰው በቁጥጥር ስር ካልዋሉት ተከሳሾች ቀጠሮ ጋር ጉዳያቸው እንዲታይና ቀጠሮ እንዲሰጥም ለግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።