በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ውድድር ለሚካፈሉ 24 ተጫዋቾች ጥሪ ቀረበ

3
አዲስ አበባ ሚያዝያ 22/2010 በግንቦት ወር ሩዋንዳ በምታዘጋጀው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያ ምርጫ 24 ተጫዋቾች ጥሪ ተደረገላቸው። በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድኑን ስትመራ የነበረችው ሰላም ዘርዓይ በሴካፋ ውድድር ላይም ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ትመራለች። በአሰልጣኟ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዎቾች መካከል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ረሒማ ዘርጋው፣ ንግሥት መዓዛ፣ሕይወት ዳንጊሶ፣ፅዮን እስጢፋኖስ፣ ታሪኳ ዴቢኮና ዙለይካ ጁሀድ ይገኙበታል። ከደደቢት እግር ኳስ ቡድን ደግሞ ሎዛ አበራ፣ መስከረም ኮንካ፣ ሠናይት ቦጋለና ትዕግስት ዘውዴ ሲመረጡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መሠሉ አበራ፣ ብዙአየሁ ታደሰ፣ ቤዛዊት ተስፋዬና ቤተልሔም ሰማን ተመርጠዋል። ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቤተልሔም ከፍያለውና አለምነሽ ደመቀ ፤ከሐዋሳ ከነማ ደግሞ አባይነሽ ኤርቂሎና ምርቃት ፈለቀ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው። ከመከላከያ ማርታ በቀለ ፣ከዲላ ከተማ ገነሜ ወርቁ ፣ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አረጋሽ ካልሳ ለውድድሩ የተመረጡ ተጫዋቾች ናቸው። እንዲሁም ከጥረት ኮርፖሬሽን ታሪኳ በርገና፣ ከአዳማ ከተማ ሴናፍ ዋቁማና ከድሬዳዋ ከነማ ደግሞ ፀጋነሽ ተሾመ በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሉሲዎቹ በሚቀጥለው ዓመት በጋና አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እየተካፈሉ ሲሆን በመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታቸው ከሊቢያ ጋር አድርገው በደርሶ መልስ 15 ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም