ቀጥታ፡

በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት አልቻልንም....የአክሱም ባለሀብቶች

ግንቦት 19/2011  በአክሱም ከተማ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ምክንያት ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ ተናገሩ።
የከተማው መስተዳድር በበኩሉ ወደ ኢንዱስትሪ ዞኑ የኤሌክትሪክ መብራት እንዲዘረጋ የ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ክፍያ ቢፈጽምም እስካሁን ተግባራዊ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል። 
የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በበኩሉ የመስመር ዝርጋታ ሥራውን በአቅርቦት ችግር ምክንያት ማከናወን እንዳልቻለ ገልጿል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን ከሰጡ ባለሀብቶች መካከል በ59 ሚሊዮን ብር ካፒታል በከተማው የቆርቆሮና ሚስማር ፋብሪካ ግንባታ ሥራ የጀመሩ ባለሃብት አቶ ሙላው ገብረዋህድ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ምክንያት የግንባታ ሥራው እንደተስተጓጎለባቸው ተናግረዋል።
እንደባለሀብቱ ገለጻ በኢንዱስትሪ ዞን የመሰረተ ልማት እጥረት በተለይ ኤሌክትሪክ ፣ ውሃ እና መንገድ አለመኖር ባለሃብቶችን እያማረረ ነው።

“የሚመለከታቸው አካላት የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡበት ይገባል” ብለዋል።

አዮዲን ጨው ለማምረት በ11 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአክሱም ከተማ ፋብሪካ የገነቡት ባለሃብት አቶ ይብራህ ለአከ በበኩላቸው፣ በዚህ ዓመት ወደ ማምረት ለመግባት ቢያቅዱም በመብራት ችግር ምክንያት ስራቸው መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
ለማሽን ተከላ እና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን የኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ መሰል መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢን ትኩረት እንዲሰጡም ጠይቀዋል። 

የአክሱም ከተማ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደማርያም መስፍን በበኩላቸው በባለሀብቶች የተነሳው ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን አምነዋል።
የከተማው መስተዳድር ለኢንዱስትሪ ዞን የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የሚውል 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለኤሌክትሪክ ኃይል አስቀድሞ ቢከፍለም እስካሁን ድረስ ሥራውን ማከናወን እንዳልተቻለ ገልጸዋል።
በአስተዳደሩ በኩል የባለሃብቶቹን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በየደረጃው ለመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
በከተማዋ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ኃላፊው ለእዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ወደከተማዋ መምጣታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማይ ግደይ በበኩላቸው በግብአት እጥረት ምክንያት ወደ ኢንዱስትሪው ዞን የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት መቸገራቸውን ተናግረዋል። 
በክልሉ የአክሱም ከተማን ጨምሮ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የኤሌክትሪክ መስመር እንዲዘረጋላቸው ተገቢውን የገንዘብ ክፍያ የፈጸሙ ከተሞችና የኢንዱስትሪ ዞኖች በርካታ መሆናቸውን አመልክተዋል። 
“በክልል ደረጃ የተጠየቀውን የኤሌክትሪክ መስመር ለመመለስ 500 ትራንስፎርመሮች ያስፈልጋሉ” ያሉት አቶ ግርማይ፣ ክልሉ በራሱ ወጪ 70 ትራንስፈርመሮችን ገዝቶ ጥያቄዎቹን በቅደም ተከተል ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስመር ዝርጋታ ቅድሚያ ለሚሹ ለጤና፣ ትምህርት እና ውሃ ተቋማት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለውን ቅሬታ ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር እየተሰራ መሆኑን አቶ ግርማይ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም