ቀጥታ፡

የተማሪዎችን የጥናትና ምርምር ክፍተቶች ማቃለል የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችያሉባቸውን የጥናትና ምርምር ክፍተቶች መቅረፍ የሚያስችል ስራ በሪፎርሙ እየተሰራ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በየዓመቱ የሚያካሂደውን የጥናትና ምርምር ቀን ለ8ኛ ጊዜ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም እንደገለጹት በአገሪቷ እየተከናወነ ባለው ሪፎርም በመታገዝ በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው።

ተማሪዎች አገር በቀልና ዓለም አቀፍ እውቀት እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት የስርዓተ ትምህርት ክለሳ እየተደረገም ይገኛል።

ክለሳው ተማሪዎች ብቃት ያላቸው፣ በአመክንዮ፣ በአርቆ አሳቢነት፣ በቴክኖሎጂ፣ በስራ ፈጠራና በስነ-ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ያስችላል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባላቸው አቅምና የትኩረት አቅጣጫ እንዲሰሩ በዘርፍ ለመክፈል እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ይህም ተቋማቱ በጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ብለዋል።

መንግስት ለትምህርት ዘርፍ 45 ቢሊዮን ብር በመመደብ እየሰራ ቢሆንም ለጥናትና ምርምር የሚመደበውን ዝቅተኛ በጀት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ወራት የዩኒቨርሲቲውን ችግሮች ማቃለል የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተግባሩ ዩኒቨርሲቲው  በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ እንደሚያስችለው ጠቅሰው በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን የሚያደርጉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲውም የያዘውን ትልቅ ራዕይ ለማሳካት በጥናትና ምርምር ስራዎች የላቀ መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

በአገሪቷ ለሰላምና ልማት ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን በጥናትና ምርምር ለመለየት ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን በመጥቀስ።

ይህም በጥናት የታገዘ ፖሊሲ በመቅረጽ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አክለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እንዲሰራም ወይዘሮ ሙፈሪያት ጥሪ አቅርበዋል።

የአንድ አገር እድገትና ጥንካሬ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተገንዝቦ ለጥናትና ምርምር የሚመደብን በጀት ማሳደግ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው።

ኢትዮጵያ ለጥናትና ምርምር የምትመድው በጀት 0ነጥብ 27 በመቶ ሲሆን ይህም በዝቅተኝነት የሚመደብ ነው።

በአለም አቀፍ ደረጃ አገራት ከአንድ ሚሊዮን ምሁራን 1 ሺ 400 ተመራማሪዎች ሲኖራቸው ኢትዮጵያ ግን 45 ተመራማሪ እንዳላት ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም ጥናትና ምርምር ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የተማረ የሰው ኃይል ወደ ኢኮኖሚው ለመቀላቀል፣ ፈጠራን ለማበረታታት፣ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እንዲሁም የተሻለ ምርትና አገልግሎት የሚጠይቅ ህዝብ ለመፍጠር ያስችላል።

ይህም ጠንካራና በኢኮኖሚ የበለፀገች አገር ለመፍጠር የራሱ አስተዋጾኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ዩኒቨርሲቲውን እ.አ.አ በ2025 ከአፍሪካ 10 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥናትና ምርምር ስራ በስፋት እንዲያከናውን በጀት የመጨመርና ከውጭ የሚገኙ በጀቶችን የማሳደግ ስራም ተከናውኗል።

ሰምንተኛው የጥናትና ምርምር ሳምንት እስከ መጪው ዓርብ የሚካሄድ ሲሆን 120 የቃልና 85 በፖስተር የተደገፉ ስራዎች ይቀርቡበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም