ቀጥታ፡

በትግራይ የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተጠቆመ

ግንቦት 19/2011በትግራይ ክልል የእስር ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደህብረተሰቡ የሚቀላቀሉ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። 

በክልሉ በማረሚያ ቤቶቹ የሚገኙ ወጣቶች የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ወደህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ኢኮኖሚያዊናማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መድረክ በአዲግራት ከተማ ተካሂዷል።

በእዚህ ወቅት የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ እንዳሉት የተለያዩ ጥፋቶችን ፈጽመው በየማረሚያ ቤቱ የሚገኙ ወጣቶች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ዳግም ወደ ጥፋት እንዳይገቡ ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

ወጣቶቹ ከእስር ሲወጡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ  በተለይ የማረሚያ ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎችና በክልሉ በየደረጃው ያሉ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በክልሉ ባሉ ማረሚያቤቶች ውስጥ ወጣት ታራሚዎች ከጥፋታቸው እንዲታረሙ እና መልካም ስብእና እንዲኖራቸው የሙያ ስልጠናና መደበኛ ትምህርት ከመሰጠቱ ባለፈ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እንዲሳተፉ ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

እንደኃላፊዋ ገለጻ ወጣት ጥፋተኞች የእስር ጊዜያቸውን አጠናቅቀው ከማረሚያ ቤቶቹ ሲወጡ የቀሰሙትን ሙያ ወደሥራ የሚቀይሩበት የገንዘብ ብድር አቅርቦት፣ የመስሪያና ማምረቻ ቦታ እንዲሁም ክትትልና ድጋፍ ስለማያገኙ ዳግም ወደጥፋት የሚመለሱባቸው አጋጣሚዎች አሉ።

“ችግሩን ለመፍታትና እንደ ዜጋ አምራች ኃይል ሆነው ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲመሩ ለማድረግ በወጣቶች ፓኬጅ ታቅፈው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሰራል” ያሉት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ንጉሰ ናቸው።

ለእዚህም ቢሮው በሥሩ ያሉ የወረዳ ጽህፈት ቤቶችና የማረሚያ ቤቶቹ  የሥራ ኃላፊዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

“ወጣቶቹን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት በመፍጠር ወጣቶቹ ባሉበት አካባቢ ወደሥራ እንዲገቡ በቢሮው በኩል ድጋፍና ክትትል ይደረጋል” ብለዋል ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ።

“በክልሉ በየማረሚያቤቶቹ ከሚገኙ የህግ ታራሚዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ ወጣቶች ናቸው” ያሉት ወይዘሮ ኪሮስ፣ በእነዚህ ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወጣቶችን አስቀድሞ ከጥፋት መከላከል መቻል መሆኑን  አመልክተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ የብድር አቅርቦትና የመስሪያ ቦታ በማዘጋጀት በልማት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደወይዘሮ ኪሮስ ገለጻ ለዕቅዱ ስኬት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ አካላትና የማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል።

ከትግራይ ማረሚያቤቶች የሥራ ኃላፊዎች መካከል የመቀሌ ከተማ ማረሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ኮማንደር አማኑኤል ፍሳሃ እንዳሉት፣ አጥፍተው ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚገቡ ወጣቶች የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡና ያለባቸውን የሙያና የቀለም ክህሎት ክፍተት እንዲሞሉ ለማድረግ ሲሲራ ቆይቷል።

“በየማረሚያቤቶቹ ከሚገኙ የህግ ታራሚዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው” ያሉት ኮማንደር አማኑኤል፣ ከእስር ቆይታ በኋላ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እስካሁንም የማረሚያ ቤቶቹ የሥራ ኃላፊዎች ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችሉ የሙያ ስልጠናዎችን ትኩረት ሰጥተው እንዲሰጡ መድረኩ መነሳሳት እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም