ሳኡዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነቷን ለማጠናከር እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2011 ሳኡዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የሳኡዲ አረቢያ አምባሳደር ሳሚ ጀ አብዱላህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው።

አምባሳደሩ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዲፕሎማቶች ትናንት ባዘጋጀው የአፍጥር ስነ-ስርአት ላይ በመታደም ለተደረገው መልካም መስተንግዶና ግብዣ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ሳኡዲ አረቢያ የቆየ ግንኙነትና ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደሩ መንግስታቸው ይህንኑ ግንኙነት የማጠናከር ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስታቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

''የኢትዮጵያ መንግስትም የሁለቱን አገሮች ግንኙነትየሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን እናምናለን'' ያሉት አምባሳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ለዚሁ ስኬት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ለመስራት ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለመስጠት ኤምባሲው ዝግጅቱን አጠናቆ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ያሉ ስራዎች እስኪጠናቀቁ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የሳኡዲ መንግስት ደስተኛ በመሆኑ ተመሳሳይ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ የረጂም ጊዜ ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ 1400 ኢትዮጵያውያን በቅርቡ መልቀቁ ይታወሳል።

የአፍጥር ፕሮግራሙ ታዳሚ የነበሩት የሶማሊያው አምባሳደር አሊ ሸሪፍ አህመድም በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ከመቼውም ጊዜ የላቀ ትብብር መፈጠሩን ገልጸዋል።

''ሁለቱ አገሮች በቀጣናዊ ትብብር፣ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የትራንስፖርትና የልማት ትብብራቸው አጋርነታቸው ተጠናክሯል'' ብለዋል።

በደህንነት ጉዳዮች፣ በኢኮኖሚክ ትብብር፣ በትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮችም ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየእለቱ ወደ ሶማሊያ በረራ እያደረገ መሆኑንም ያነሱት አምባሳደሩ ''በቀጣይም ለሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነት እንሰራለን'' ብለዋል።

አምባሳደሮቹ የኢትዮጵያ መንግስት ላዘጋጀው የአፍጥር ፕሮግራም ምስጋናቸውን አቅርበው አጋጣሚው ከበርካታ አገሮች ዲፕሎማቶች ጋር የሚገናኙበት ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም