የመረብ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል

ግንቦት 19/2011 የሐበሻ ሲሚንቶ የወንዶች መረብ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።
ትናንት ወላይታ ሶዶ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ መከላከያን በአራት የጨዋታ መደብ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል።

ሮቤ ላይ መዳወላቡ ዩኒቨርስቲ አዲስ አበባ ፖሊስን በአራት የጨዋታ መደብ 3 ለ 1 ሲያሸንፍ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም በተካሄደ ጨዋታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽን በሦስት የጨዋታ መደብ 3 ለዜሮ ረቷል።

ከትናንት በስቲያ በአራት ኪሎ በሚገኘው የስፖርት ጅምናዚየም ሙገር ሲሚንቶና ጣና ባህርዳር ባደረጉት ጨዋታ ሙገር ሲሚንቶ ተጋጣሚውን  3 ለ ዜሮ አሸንፏል።

ፕሪሚየር ሊጉን ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ ሲመራ መዳወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ29፣ ሙገር ሲሚንቶ በ23 ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃ ይዟል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተካሄደዋል።

ትናንት ቡታጅራ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቡታጅራ ከተማን 33 ለ 17 ሲያሸንፍ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ፌዴራል ፖሊስ ጎንደር ከተማን 35 ለ 29  አሸንፏል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከመከላከያ ጋር ባደረገው ጨዋታ 26 ለ 26 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም በተደረገ ሌላ ጨዋታ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 28 ለ 26  አሸንፏል።

ትናንት ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማና ከምባታ ዱራሜ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ በመግለጹ ከምባታ ዱራሜ በፎርፌ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 አሸናፊ መሆኑን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ሳምንታት የውድድር መርሃ ግብር ከድሬዳዋ ከተማ ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በውድድሩ ደንብ መሰረት የፎርፌ ውጤት እንደሚያገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ድሬዳዋ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ውድድር እንደማይሳተፍ ማሳወቁን ተከትሎ በፕሪሚየር ሊጉ የሚጫወቱ የእጅ ኳስ ክለቦች ቁጥር ወደ ዘጠኝ ዝቅ ብሏል።

የፕሪሚየር ሊጉን ደረጃ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ26 ነጥብ ሲመራ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ22 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ20 ነጥብ ሁለተተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም