በወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ደቡብ ክልል አሸናፊ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ደቡብ ክልል አሸናፊ ሆኑ

ግንቦት 19/2011 የኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በወንዶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሴቶች የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሆኑ።
ከግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ የወጣት ማዕከል ሲካሄድ የነበረው የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ትናንት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በወንዶች ከ54 ኪሎ ግራም በታች እስከ 74 ኪሎ ግራም በታች፣ በሴቶች ከ46 ኪሎ ግራም በታች እስከ 67 ኪሎ ግራም በታች ያሉት ሻምፒዮናው የተካሄደባቸው የውድድር ዘርፎች ናቸው።
ከአምስት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች 35 ወንዶችና 31 ሴቶች በሻምፒዮናው ተሳትፈዋል።
ትናንት በውድድሩ መዝጊያ ላይ ከ49 ኪሎ ግራም በታች ሴቶች ግጥሚያ የቤኒሻንጉል ጉምዟ ሌሊሴ ኡፌራ የአማራ ክልሏን ሰብለ ፈለቀን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ተጋጣሚዋ ሰብለ የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።
በዚሁ የክብደት ዘርፍ በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት የደቡብ ክልሏ ውብዓለም በየነ እና የኦሮሚያዋ ሶፊያ በለጠ የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
ከ58 ኪሎ ግራም በታች ወንዶች የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳዳሪ የሆነው ዘሪሁን ወልዴ የአማራ ክልሉን ዮሐንስ ዘመነን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ተሻላሚ ሲሆን ዮሐንስ የብር ሜዳሊያ አግኘቷል።
በዚሁ የክብደት ዘርፍ የግማሽ ፍጻሜ ላይ የተሸነፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ ኤርሚያስ አሰፋና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተወዳዳሪ ኑረዲን መሐመድ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና በወንዶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል እና የደቡብ ክልል በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።
በሴቶች የደቡብ ክልል አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል።
በወንድ የደቡብ ክልል ተወዳዳሪ የሆነው ሲያንሰው ዘኪ በሴት የአማራ ክልል ተወዳዳሪ የሆነችው አክሱማዊት ፍስሀ ኮከብ ተጫዋች ሆነው ተመርጠዋል።
በአጠቃላይ የሻምፒዮናው አሸናፊዎችና ኮከብ ተጫዋቾች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል።
የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት አስፋው እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተዘጋጀውን ሽልማት ለተወዳዳሪዎቹ አበርክተዋል።
የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ክልሎች በፋይናንስ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት በሻምፒዮናው ላይ እንደማይሳተፉ ለኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን አሳውቀው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ የሻምፒዮናው ዋና ዓላማ እንደነበረ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
በ2009 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በተካሄደበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል በሁለቱም ጾታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደነበረ የሚታወስ ነው።