መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች የአፍጥር ፕሮግራም ተከሄደ - ኢዜአ አማርኛ
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች የአፍጥር ፕሮግራም ተከሄደ
ግንቦት 19/2011 መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የአፍጥር ፕሮግራም ትናንት ተከናወነ።
በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የታደሙ ሲሆን በኢትዮጵያዊ መስተንግዶ አፍጥረዋል።
በአፍጥር ስነ-ስርዓቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተገኝተው ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያ በሃይማኖት ብዝሃነት፣ በመቻቻልና ተከባብሮ በመኖር ልዩ መገለጫ ያላት አገር መሆኗንም አስረድተዋቸዋል።
በእስልምና ሃይማኖት ታሪክ በአረቦች እንዲሁም በነብዩ ሙሀመድ ልዩ ስፍራ የሚሰጣት ሲሆን የመጀመሪያውን አዛን ያሰማው ሙአዚን ኢትዮጵያዊ ቢላል (ቢላል አል- ሃበሽ) መሆኑም ለዚሁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ልዩ የሚያድርጓትን በርካታ መገለጫዎች እንዳሏት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለአምባሳደሮቹ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
የረመዳን ወር በሙስሊም ማህበረሰብ ዘንድ ታላቅ ስፍራ እንዳለው የገለጹት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ''ይህ አጋጣሚም ከመላው የዓለም ማህበረሰብ ጋር ያለንን ትብብር ይበልጥ በማጠናከር በጋራ ለመስራት የተዘጋጀንበት ወቅት ነው'' ብለዋል።
ኢትዮጵያ ድህነትን ለማጥፋት፣ ዴሞክራሲን ለማጎልበትና ሰብአዊ መብት በማክበር ሂደት ስኬታማ ለመሆን በሚያስችል የለውጥ ሂደት ላይ እንደምትገኝም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን ኢትዮጵያ በመቻቻል እሴቶቿ ለአለም ምሳሌ መሆኗን ጠቅሰው የተዘጋጀው የአፍጥር ስነ-ስርዓት ለእሴቱ እውቅና መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
በርካታ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ያሏት አገር መሆኗን በማንሳት የዝግጅቱ ታዳሚዎች ጊዜ በሚያገኙበት ወቅት አገሪቱን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
በእለቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስን ጨምሮ ሌሎች ኡለማዎች በመድረኩ ላይ ታድመዋል።