ቀጥታ፡

ለ2012 ምርጫ ውጤታማነት ሰላምን ማስፈንና ተፈናቃዎችን ወደ ቀያቸው መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል-ፓርቲዎች

ግንቦት 18/2011ኢትዮጵያ በ2012 ለምታካሂደው ምርጫ ውጤታማነት ሰላምና መረጋጋትን ማስፈንና የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።
ህገ መንግስቱ በየአምስት አመቱ ምርጫ መካሄድ አንዳለበት በሚያስቀምጠው መሰረት አገሪቷ በ2012 ዓ.ም ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ሰላም ከሆነች ለምርጫው ዝግጅት ለማድረግ የቀረው ጊዜ በቂ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ መካሄዱ ላይ ይስማማሉ።

ይሁንናአሁን በአገሪቷ ባለው የጸጥታ ችግርና የዜጎች መፈናቀል ለህዝብ አማራጭ ሃሳቦችን በማሳወቅ ምርጫ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ ሊቀመንበር  አቶ አህመድ ሃጂ ገመዳ እንደተናገሩት ፓርቲያቸው በተለያዩ ወረዳዎች ጽህፈት ቤት በመክፈት ለምርጫ ዝግጅት እያደረገ ነው።

በተለያዩ ዘርፎች አማራጭ ፖሊሲዎችን በመንደፍ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተከታታይ ውይይት ለማድረግም ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች እቅዳቸውን ለህዝብ ተዘዋውሮ ለማሳወቅ የአገር ሰላም ቅድሚያ መሰጠት አንዳለበት ገልጸው ሰላም ካለ ምርጫው በህገ መንግስቱ መሰረት በወቅቱ መካሄዱ ላይ እንደሚስማሙ ነው አቶ አህመድ የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረንስ ዋና ጸሃፊ አቶ ግርማይ ሃደራ በበኩላቸው ዜጎች በየቦታው ተፈናቅለውና በተወሰኑ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እያለ ምርጫ ማካሄድ ውጤታማነቱ ላይ ችግር ይፈጥራል ይላሉ።

ምርጫ የህዝብ በመሆኑ መራጩ ህዝብ ሳይረጋጋና ሰላም ሳይኖር መካሄዱን እንደማይደግፉም በመግለጽ ሃሳበችውን ያጠናክራሉ።

በመሆኑም የተፈናቀሉ ዜጎችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀያቸው መመለስና አገርንና ህዝብን የማረጋጋት ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ጨምረዋል።

ሰላምን ለማስፈንና ህዝቡ የሚጠቅመውን ፓርቲ ተረጋግቶ እንዲመርጥ ጊዜ ያስፈልገዋልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነ "በመርሃ ግብራችን መሰረት አላማችንን ለማስተዋወቅ ጊዜ አይወስድብንም" በማለት ለምርጫ የቀረው ጊዜ በቂ እንደሆነና በወቅቱ ቢካሄድ በፓርቲው ላይ ተጽእኖ እንደማይኖረውም ያነሳሉ።

የጉራጌ ህዝባዊ ንቅናቄ ጊዜአዊ ሊቀመንበር አቶ ቴዎድሮስ ኮሬ በበኩላቸው አላማቸውን ለደጋፊዎቻቸው ለማሳወቅ ቀዳሚው ሰላም በመሆኑ ፓርቲያቸው በአገራዊ አንድነትና ሰላም ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎች ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ቢካሄድ እንደማይቃወሙ የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ አሁን በአገሪቷ ካለው አለመረጋጋት አንጻር ግን ቀዳሚው ጉዳይ በምርጫ የመወዳደርና የማሸነፍ ጉዳይ መሆን የለበትም ይላሉ።

ቅድሚያ የሚሰጠው የአገሪቷ ሰላም በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫ ቢካሄድ ከምርጫው በኋላ ጥሩም መጥፎም ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ከምርጫው በኋላ የተሻለ ሁኔታ እንዲኖር በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጀመሩ ስራዎች መጠናከር አለባቸው የሚል አስተሳሰብ አላቸው።

እንደ ፓርቲ ለምርጫ ለመዘጋጀት ያለው ጊዜ በቂ ቢሆንም እንደ አገር ያለው የሰላም ሁኔታ በተለይም ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ አላማን ለማሳወቅ ወሳኝነት አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው በሚደረገው ዝግጅትና ምርጫን ለማካሄድ በአገሪቷ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ከሆነ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳውቃለሁ ማለቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም