ግብርና ዘርፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ግብርና ዘርፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር የሚያስችሉ ስራዎች ይሰራሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
ግንቦት 18/2011 የግብርና ዘርፍን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የግብርና ንቅናቄ መድረክ ላይ ተገኝተው በሠጡት ማብራሪያ በመጭዎቹ ዓመታት ግብርና የአገሪቷ ዋነኛ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ምሰሶ ሆኖ እንዲቀጥልና ለውጤት እንዲበቃ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ፣ የተቋምና የበጀት ማጠናከር ተግባራት በስፋት በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።
በመጪው በጀት ዓመት ከየትኛውም የምጣኔ ሀብት ዘርፍ በበለጠ ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ በጀት የሚመደብ መሆኑንም አንስተዋል።
በተለይ ምርታማነትን በከፍተኛ መጠን ማሳደግ እንዲቻል ወሳኝ የሆነውን የአነስተኛ መስኖ ልማት ለማጎልበት በመጪው በጀት ዓመት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ሀብት እንዲመደብ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አንስተዋል።
ከዚህም ሌላ በአገሪቷ ያለውን የእርሻ መሬት በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ሰፋፊ የንግድ እርሻ ልማቶችን ለማሳደግ የፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
የግብርናግብዓት አቅርቦት፣ የሎጂስቲክና ሌሎች ችግሮችን ለመከላከልም መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ዶክተር አብይ በተለይም የማዳበሪያ አቅርቦትን በአገር ውስጥ ለመሸፈን ተስፋ ሰጭ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አውስተዋል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የምግብ እጥረት ውስጥ የሚገኘውን 20 ሚሊዮን ያህል ዜጋን ለመታደግ ብሎም አገሪቷ ለመግብ እርዳታ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ወጭ ለማስቀረትና በአጠቃላይ የአገሪቷን ምጣኔ ሐብት ለማጠናከር የአርሶ አደሩና የዘርፉ ባለሙያዎች ሚና ግንባር ቀደም መሆኑን አስገንዝበዋል።
"የታሰቡት ሰፋፊ የግብርና ልማት እቅዶች ሊሳኩ የሚችሉ ናቸው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከአንድ ዓመት በፊት ሊሳኩ ቀርተው ለማሰብ የሚከብዱ የነበሩት የፖለቲካ፣ የማህበራዊና የምጣኔ ሐብት ስኬቶች ስንቅና ኃይል ሊሆኑን ይገባልም" ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በመጪው ክረምት 4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል የተያዘውን መርሃ-ግብርም ችግኝ በመትከል አስጀምረዋል።