ቀጥታ፡

በባህርዳር ከተማ በባጃጅ ተሽከርካሪ የታገዘ ዝርፊያና ድብደባ የነዋሪዎች ስጋት ሆኗል

ግንቦት 17/2011 በባህር ዳር ከተማ በጨለማን ተገን የሚፈጸም በባጃጅ የታገዘ ዝርፊያና ድብደባ ሰላማቸውን በመንሳት ስጋት እንደሆነባቸው የከተማው ነዋሪዎች ተናገሩ።

የክልሉና የከተማው  የስራ ኃላፊዎች በሰላም፣መልካም አስተዳደርና ልማት ዙሪያ ከባሀር ዳር ከተማ  ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ነዎሪዎቹ እንዳሉት አሁን በባህር ዳር ከተማ ሰዎች በቡድን እየተዘረፉና አለፍ ሲልም የግድያና የድብደባ ወንጀሎች እየተፈጸመባቸው ነው።

መምህር ይበልጣል ሰውነት የተባሉት ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በከተማው ወንጀል የሚፈፅሙ ቡድኖች እየተበራከቱ መጣታቸውን ተናግረዋል።

 በቡድኑ የግለሰቦችን የጣት ቀለበት ሳይቀር ዝርፊያ እየፈፀሙ ይገኛል።

ለወንጀሉ መፈጸሚያ ዋና መሳሪያዎች ባለ ሦስት እግር ባጃጆችን በመጠቀም እንደሆነ ጠቅሰው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

አሁን በከተማው የህግ የበላይነት እየተሸረሸረ በመምጣቱና የባህርዳርን  መልካም ስም የሚያጉድፉ ስራዎች እየተፈጸሙ በመምጣታቸው መንግስት ለጉዳዩ  ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ባጃጅ ተሽከርካሪዎችእንደ ባህር ዳር ከተማ ዋነኛ የወንጀል መፈጸሚያ መሳሪያዎች መሆናቸውን የተናገሩት ደሞ  አባ ገብረ ሥላሴ ዮሃንስ ናቸው።

"ለዚህ ምክንያቱ የመንግስት የቁጥጥር መላላት ነው" ብለዋል።


እንደሳቸው ገለጻ ህብረተሰቡ ጠዋት  ቤቴ ክርስቲያን ለመሳለም በማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።


መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከመስራት በፊት የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንዲሚገባ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ጽጌ  በበኩላቸው በክልሉ ውስጥ የሚካሄድን ህገወጥ እንቅስቃሴ ለመግታትና ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ ለጸጥታ ኃይሉ ስምሪት መሰጠቱን አስታውቀዋል።


በተለይም በባጃጅ የሚደረግን የቡድን ዝርፊያ ለማስቆምና ወንጀለኞችን በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ትኩረት መሰጡን ገልጸዋል።

ትናንት ምሽት ብቻ በተካሄደ ስምሪት 89 የዝርፊያ ባጃጆችን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ነው ብርጋዴል ጀነራል አሳምነው ያስረዱት።


የባህር ዳር ከተማን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ ከተሞች የሚካሄድን የቡድን ዝርፊያ ለማስቆም የክልሉ የጽጥታ ኃይል በልዩ ትኩረት ወደ ስራ ገብቷል።

"ትላልቅ ተሽከርካሪዎችን ሳይቀር በቀን የመዝረፍ ሙከራዎች እየተከናወኑ በመሆኑ  የጸጥታ ኃይሉ ህግን ለማስከበርና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ተገቢውን እርምጃ ይወስዳል "ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉ ቀን አየሁምችግሩን ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የህብረተሰቡ ትብብር አናሳ በመሆኑ ባጃጆች ከተፈቀደላቸው መዳረሻ  ውጪ የወንጀል ድርጊት እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ አቅሙ በፈቀደ ህገ-ወጦችን በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት መተባባር  ሲገባ ችግሩን ለመንግስት ብቻ መተው ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።


መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ከህዝብ በሚደርሰው መረጃና ማስረጃ ላይ በመነሳት ህግን የማስከበር ተግባሩን እንደሚወጣ ተናግረው ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ  ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።


የከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በመሆንበወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፣የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃለፊዎችና የኃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም