በታሪክ የተሳሰረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ማቆየት ይገባናል - ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ - ኢዜአ አማርኛ
በታሪክ የተሳሰረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ማቆየት ይገባናል - ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ
አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 ''ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ታሪክ የተሳሳረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለማቆየት ባህላችንንና ታሪካችንን ጠብቀን ማቆየት ይገባናል'' ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናገሩ።
የሲዳማ ዘመን መለወጫ ''ፊቼ ጫምባላላ'' ዋዜማ ዛሬ በአዲስ አበባ ኦሮሞ ባህል ማዕከል ተከብሯል።
በዓሉ መጠሪያውን ያገኘው በየዓመቱ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በሚከበርበት ቀን ባህላዊ ምግብ ይዛ ዘመድ አዝማዶቿን ትጠይቅ በነበረች 'ፊቾ' ከምትባል ሴት ነው።
በቆጮና በቅቤ የሚሰራ 'ቡርሳሜ' የተሰኘ ባህላዊ ምግብ አዘጋጅታ ዘመድ አዝማድ የአካባቢው ህብረተሰብ ሰብስባ ትመግብ የነበረችውን ይህቺ ሴት በሞት ስትለይ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል በስሟ ፊቼ ተብሎ መሰየሙን የበዓሉን መከበር አስመልክቶ በቀረበ የመወያያ ጽሁፍ ተገልጿል።
የፊቼ ጫምባላላ በዓል መከባባርና መቻቻል እንዲሰፍን፣ እርቅ እንዲወርድ፣ ልማት እንዲፋጠንና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጎሳ መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች ትምህርት የሚሰጡበት መድረክ እንደሆነ ተነግሯል።
በተለይም የተጣሉ ሰዎች ቂምንና በቀልን ይዘው ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሄዱ የአገር ሽማግሌዎች በዓሉ ከመከበሩ ሁለት ወር አስቀድመው ለእርቀ ሰላም የሚተጉበት ጊዜ መሆኑ ተነግሯል።
በተጨማሪ ሰዎች በጋራ የሚመገቡበት ሴቶችና አረጋውያንና ሰራተኞች ከስራ አርፈው የሚውሉበት አንስሳትና እጽዋት በእለቱ የተለየ ውሃና ምግብ ተሰጥቷቸው ደሰ ብሏቸው የሚያሳልፉበት ጊዜ ነው።
በዓሉ በየትኛው ወርና ቀን እንደሚውል አያንቶ ተብለው የሚጠሩ ባህላዊ ሊቃውንት የጨረቃ ምልክትና ኮከብ ቆጠራ ስሌትን በመጠቀም ወስነው ለህዝቡ ከበዓሉ አንድ ሳምንት በፊት ቀኑን ያውጃሉ።
የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲከበር ምክትል ከንቲባው እንዳሉት፤ ዘመን ተሻጋሪ በሆነ ታሪክ የተሳሳረውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለማቆየት ባህላችንንና ታሪካችንን ጠብቀን ማቆየት ይገባናል።
‘’በተለይ ያቆራኘን፣ ያስተሳሰረንና ችግሮቻችንን በጋራ እንድንሻገር ጉልበት የሆነን ታሪካችንን ለትውልድ በማስተላላፍ ከታሪክ ተወቃሽነት ራሳችንን ማዳን አለብን'' ብለዋል።
''አባቶቻችን ያቆዩትን አንድነትና አብሮ የመኖር እሴቶች ለትውልድ ለማቆየት ባህላችንንና ታሪካችንን መጠበቅ ይገባናል'' ሲሉም አክለዋል።
የጋራ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህል እና ታሪክ የምታንፀባርቅ ከተማ መሆን እንዳለባት የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፤ ''የሲዳማ ህዝብም በከተማዋ ማንነቱና ታሪኩ እንዲታይ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል'' ብለዋል።
''የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችውን አዲስ አበባ ለማልማትም እየታየ ካለው አላስፈላጊ ንትርክና ጎታች አለመለካከት ለማላቀቅ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት'' ብለዋል።
የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫውቻ በበኩላቸው በትውልድ ቅብብሎሽ የመጣውን ህዝባዊ ባህልን ጠብቆ ማቆየት የትውልዱ ሃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል።
በበዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት የተራራቁ የሚቀራረቡበት በመሆኑ ትውልዱ እሴቶቹንና ጸጋዎችን ጠብቆ ማቆየት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በዓሉ ግንቦት 22 እና 23 በሃዋሳ እንደሚከበር ተናግረዋል።
በዛሬው መድረክ አባገዳዎች፣ የሲዳማ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በመድረኩም ባህሉን አስመልክቶ የመወያያ ጽሁፍና በፊቼ ጫምባላላ የሚቀርቡ የባህላዊ ምግቦች ዙሪያ ገለጻዎች ቀርቧል።