ዩኒቨርሲቲው 49 የህክምና ዶክተሮች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው 49 የህክምና ዶክተሮች አስመረቀ
ደብረ ማርቆስ ግንቦት 17 / 2011 የደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ 49 የህክምና ዶክተሮች ዛሬ አስመረቀ።
ዩኒቨርሲቲው ለሦስተኛ ጊዜ ያስመረቃቸው ሐኪሞች ከሥራ ዓለም ወደ ሥልጠና ገብተው ለአምስት ዓመታት በሙያው መሰልጠናቸው በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።
የዩኒቨርስቲው ጥሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በመተባበር በሰጠው ስልጠና ሰልጣኞቹ ለምረቃ በቅተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ሲቀበል በቂ የማስተማሪያ ግብዓቶችና ምቹ ሁኔታዎች እንዳልነበሩ ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ሆኖም በአገር ደረጃ ያለውን የሕክምና ባለሙያዎች እጥረት ለማቃለል ያደረገውን ጥረት እንዳሳካ ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው እያስገነባ ባለው የጤና ካምፖስ የማስተማሪያ ሆስፒታል ለመገንባት የዲዛይን ሥራውን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ለተመራቂዎቹ ''ሐኪም ሆናችሁ ስትኖሩ ብዙ ሀብት ንብረት ላይኖራችሁ ይችላል። ነገር ግን ማህበረሰብን በጎነት ማገልገል ከገንዘብ የላቀ እርካታ ስለሆነ በጎ ሆናችሁ በሙያችሁ ማገልገል ይጠበቅባችኋል'' ብለዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ዶክተር ብርሃኑ ስሌማን እንዳለው ከመንግሥትም ሆነ ከሌላው አካል ሳይጠብቁ የራስ ዝግጅትና ጥረት ከታከለበት የሚከብድ ነገር እንደሌለ ገልጾ፣በሙያው ለመመረቅ የበቃው የጊዜ አጠቃቀም ባህሉን በመለወጥና በዓላማ ጽናት እንደሆነ ተናግሯል።
ዶክተር ደባስ ደስያለው በበኩሉ የማህበረሰቡ የሕይወት መድን በሆነው ሙያው ኅብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
ዩኒቨርሲቲው በጤናው መስክ ማስተማር ከጀመረ ከ2004 አንስቶ የዛሬዎችን ሳይጨምር 80 ሐኪሞችን አስመርቋል።