ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መህመት “አፍሪካን ለዜጎቿ ምቹ ለማድረግ በጋራ መነሳት አለብን” አሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 የአፍሪካ ህብረት የተመሰረተበትን 56ኛ ዓመት በምናከብርበት በዚህ ወቅት “የምንፈልጋትን አፍሪካ” እውን ማድረግ የምንችለው አጀንዳ 2063 ተግባራዊ በማድረግ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መህመት የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት በዛሬው እለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ከዛሬ 56 አመት በፊት አዲስ አበባ ላይ የተሰባሰቡና ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡ 32 አገሮች ከፍ ያለ ክርክር በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መስርተዋል።

ለክፍለ ዘመን የዘለቀውን የበላይነት፣ ብዝበዛ፣ ባርነትና ግዞት ለመጣል ጥንካሬዋን ተገንዝባ ከእንቅልፏ የነቃችው አፍሪካ ህብረትና ክብር የሚገኘው በመከባበር መሆኑን በማወቋ ሃይሏን ለማስተባበር ችላለች በማለት ተናግረዋል።

አፍሪካ ሙሉ በሙሉ ነጻ ወጣች እንዲሁም ህብረቷ እውን ሆኗል የምንለው ያሉብንን ችግሮች ስናስወግድ ነውም ብለዋል።

ይህ የሚሳካው ደግሞ የእያንዳንዱ አፍሪካዊ ህይወት ሰላም የተሞላበት፣ የትምህርት እድል የተመቻቸለት፣ አካላዊና አእምሮአዊ ጤንነቱ የተሟላ ሲሆን፣ የስራ እድል ሲያገኝ፣ ማህበራዊና ባህላዊ እድገቱ ሲረጋገጥና መሰረታዊ መብቱን የሚያስከብር መልካም አስተዳደር ሲሰፍንለት ብቻ ነው ብለዋል።

የዚህ አመት የአፍሪካ ቀን የሚከበረው ስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾች እና የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለሟቋቋም መፍትሄ መሻት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

መሪ ቃሉ የገጠመንን ፈተና በግልጽ ከማሳየቱ በላይ ጊዜ ሳንፈጅ በጋራ በመነሳት አፍሪካውያን በነጻነት እንዲኖሩ፣ ስብዕናቸው እንዲከበርና አምራች እንዲሆኑ መስራት እንዳለብን ያሳያል።

የአፍሪካ መንግስታት ይህን እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ሊቀመንበሩ ለጋሽ ድርጅቶችን በማመስገን ለስደተኞቹና ከስደት ተመላሾች የሚያደርጉትን ልገሳ በእጥፍ እንዲያሳድጉም ጠይቀዋል።

መንግስታትም ከስደት ተመላሽ ዜጎቻቸውን መብት በማክበርና ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በአጋጣሚውም ስደተኞችን ተቀብለው በማስተናገድ ላይ ያሉ አገራትን አመስግነዋል።

የበለጸገች፣ሰላሟ የተረጋገጠና የጋራ አፍሪካን መመስረት የሚቻለው የጋራ ራዕያችንን እውን በማድረግ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ በአለም መድረክ የምንታይበትን አስተሳሰብ መለወጥ የሚችሉት ዜጎቿ ብቻ ናቸው ነው ያሉት።

"በተፈጥሮ ሐብት የታደለችው ግን ብዙ ድሆችን ታቅፋ የያዘችውን አህጉራችንን መቀየር የምንችለው በመተባበር ብቻ ነው፤ ውቅያኖሶች የሚበሏቸውን ወጣት ልጆቻችንን የሽግግራችንና የዕድገታችን ማዕዘን ማድረግ አለብን" ብለዋል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እሳቤም ፍሬ እያፈራ ሲሆን የጋራ ብልጽግና እንደሚያጎናጽፈን እናምናለን ብለዋል።

በዚህም የአለም የንግድ ዋነኛ አጋር መሆንም እንችላለን ያሉት ሊቀመንበሩ ከዚህ በተጨማሪ አፍሪካን እንዲያስተሳስሩ የያዝናቸው የሰዎች ነጻ ዝውውርና አንድ የአፍሪካ ፓስፖርትን እውን የማድረግ ፕሮጀክት ለማሳካት መትጋት ይጠበቅብናል በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአፍሪካ ለስራ ፈጠራ የሚያግዙንን የግብርና ምርታማነትን፣ ጥሬ እቃ ማቀነባበርን፣ የምርት ስብጥርን፣ ስልጠናን፣ የሰው ሃብታችንን ቀጣይነት ባለው መልኩ ማብቃት፣ የመሰረተ ልማት ትስስርን ማስፋት፣ ኢንዱስትሪን ማስፋፋትና እምቅ የሃይል አማራጭ በማጎልበት ለወጣቶችና ለሴቶች አጠቃላይ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል።

ይህንኑ ግብ ለማሳካት አፍሪካዊ የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ከሁሉ በላይ መንግስታት ህዝቡን በማነቃነቅ ለስኬቱ እንዲተባበሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህ መንገድ ጥረታችንን አስተባብረን ከተጓዝን መሰናክሎችን በማለፍ ጥንካሬያችንን በማጎልበት የራሳቸንን እጣ ፋንታ ራሳቸን መወሰን እንችላለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም