ቀጥታ፡

በመድሃኒት አስመጪነትና ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩ 13 ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ከገበያ ወጥተዋል

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 በመድሃኒት አስመጪነትና ማከፋፈል ሥራ የተሰማሩ 13 ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መዘጋታቸውን የኢትዮጵያ ምግብ፣ መድሃኒት፣ ክብካቤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ። በባለስልጣኑ የደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ሲሳይ እንዳሉት ኩባንያዎቹ የንግድ ፍቃዳቸውን መልሰው ሥራቸውን ያቋረጡት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ  እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ብቻ በመድሃኒት አስመጪነትና አከፋፋይነት ዘርፉ ለመሰማራት 79 ድርጅቶች ፍቃድ ማውጣታቸውንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 377 ኩባንያዎች በዘርፉ ተሰማርተው እንደሚገኙም ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የሥራ ፍቃዳቸውን ከመለሱ ኩባንያዎች መካከል ሶስቱ በሰጡት አስተያየት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራቸውን ለማቋረጥ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል። የወዝ ትሬዲንግ የገበያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢንያም ከበደ እና ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉት የቀድሞ ባድማስ ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ መድሃኒት ከውጭ ሀገራት ማስመጣት አልቻሉም። ችግሩን ለማቃለል በብሄራዊ ባንክ በኩል የሚገባውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል። በመሆኑም ኪራይን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን በመቸገራቸው ከገበያው መውጣታቸውን ነው የገለጹት። በፋርማቴክ ትሬዲንግ የቴክኒክ ኃላፊና ሥራ አሰኪያጅ  አቶ ቢንያም አሰግድ ኩባንያው የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን ለመፍታት ከአንድ ዓመት በላይ ጥረት ቢያደርግም ውጤት ማግኘት አልተቻለም ብለዋል። በዚህ ተስፋ መቁረጥም ለረጅም ዓመታት በዘርፉ የቆዩ አንጋፋ ባለሙያዎችን በትነው ኩባንያቸውን መዝጋታቸውን ገልፀዋል። የሪያሌብል ጀነሬት ሜዲካል ትሬዲንግ ባለቤት  ዶክተር ተስፋዬ ገብረኪዳን በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በመድሃኒት አስመጪነትና ማከፋፈል ስራ የሚያበረታታና ምቹ ሁኔታ የሌለው በመሆኑ በቅርቡ ከገበያው ለመውጣት ማቀዳቸውን ነው የገለጹት። የኢዜአ ሪፖርተር  በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ከውጭ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ችግር በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን አስተያየት ለማካተት  ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም