ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ በናይጄሪያና ካናዳ በሚካሄዱ ውድድሮች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ በናይጄሪያና ካናዳ በሚካሄዱ ውድድሮች ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 17/2011 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዛሬ በናይጄሪያና ካናዳ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ይሳተፋሉ
በናይጄሪያ ኢዶ ግዛት በሚካሄደው የኦክፔክፔ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች አትሌት ስንታየሁ ለወጠኝ እና አትሌት ሱቱሜ አሰፋ በወንዶች አትሌት ታዬ ግርማ ይሳተፋሉ።
በውድድሩ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች የማሸነፍ ግምቱን እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዘገባ ያመለክታል።
በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸነፉ አትሌቶች የ20 ሺህ ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በአጠቃላይ ከአንድ እስከ ስምንተኛ ለሚወጡ አትሌቶች የ112 ሺህ ዶላር ሽልማት ተዘጋጅቷል።
ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደው የኦክፔክፔ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የብር ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
በባለፈው ዓመት የኦክፔክፔ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች አትሌት ደራ ዲዳ እና በወንዶች ኬንያዊ አትሌት አሌክስ ኪቤት አሸናፊ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል በካናዳ የኦቶዋ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ምሽት 12 ሰአት ከ 30 ይካሄዳል።
በሴቶች አትሌት ጌቴ አለማየሁ እና አትሌት እመቤት መንግስቱ በወንዶች አትሌት ፍቃዱ ሀፍቱ ይሳተፋሉ።
በሁለቱም ጾታዎች ኬንያውያን አትሌቶች የማሸነፍ ቅድሚያ ግምቱን እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።
በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች 5 ሺህ የካናዳ ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን ከአንድ እስከ ስምንት ለሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
ለ34ኛ ጊዜ በሚካሄደው የኦቶዋ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
በባለፈው ዓመት የኦቶዋ 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በሴቶች አትሌት ነጻነት ጉደታ በወንዶች አትሌት ልዑል ገብረስላሴ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
በተጨማሪም ነገ በካናዳ በሚካሄደው በኦቶዋ ማራቶን በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት እንዳገኙ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።
በሴቶች አትሌት ሹኮ ገነሞ፣ አትሌት አበባ ገብረመስቀል፣ አትሌት ቤተልሄም ሞገስና አትሌት ትዕግስት ግርማ ይሳተፋሉ።
የኦቶዋ ማራቶንን ታሸንፋለች ተብላ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አትሌት ትርፌ ጸጋዬ በገጠማት የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ሳቢያ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በውድድሩ ላይ እንደማትሳተፍ አስታውቃለች።
በሴቶች ላለፉት ዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት በኦቶዋ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማሸነፍ የበላይነቱን ይዘዋል።
በወንዶች ባለፈው ዓመት በኔዘርላንድ ሮተርዳም ማራቶን 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱን ያስመዘገበው አትሌት አበራ ኩማ የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝቷል።
አትሌት ጽዳት አበጀ፣ አትሌት ጌቱ ፈለቀ እና አትሌት አዱኛ ታከለ ከአትሌት አበራ ኩማ በተጨማሪ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ አትሌቶች የ30 ሺህ ዶላር ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ አስር ለሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
ለ45ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኦቶዋ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።
በባለፈው ዓመት የኦቶዋ ማራቶን በሴቶች አትሌት ገለቴ ቡርቃ በወንዶች አትሌት የማነ ጸጋይ አሸናፊዎች ነበሩ።