ቀጥታ፡

ክለቡ ለኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ማለፉን አረጋገጠ

መቐለ ግንቦት17/ 2011 የመቐለ 70 እንደርታ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ማለፉን አረጋገጠ።

የክለቡ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሕይወት ዐረፋ ዓይነ እንደገለጹት ክለቡ በመጪው ዓመት በሚካሄደው ሊግ ተሳታፊነቱን ያረጋገጠው ይወዳደርበት በነበረው ሁለተኛ ዲቪዚዮን 26 ነጥብ ይዞ በማጠናቀቁ ነው።

ክለቡ  በሊጉ በሚያደርጋቸው ውድድሮች በፍቅርና በአንድነት ስሜት ለመወዳደር መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ክለቡ ውድድሩን በመሪነት 27 ነጥብ በመያዝ በአንደኛነት ካጠናቀቀው የሻሸመኔ ሴቶች እግር ኳስ ክለብ ጋር የዋንጫ ጨዋታ  በመጪው ቅዳሜ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

ክለቡ ተጋጣሚውን በማሸነፍ ዋንጫውን ለመውሰድ መዘጋጀቱንም ኢንስትራክተር ሕይወት ተናግረዋል።

የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ድጋፉን እንዲሰጣቸውም አሰልጣኟ ጠይቀዋል።

የመቀሌ ከተማ አስተዳደር ክለቡን በሃሳብ፣በገንዘብና በትጥቅ ለማጠናከር እየደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የመቀሌ ሰባ እንደርታ የወንዶች እግር ኳስ ክለብ በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን ከሚመሩት ክለቦች አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም