በወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል
ግንቦት 16/2011 ትናንት በተጀመረው የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ዛሬ ሶስት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተደርገዋል።
በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ የወጣት ማዕከል የሚካሄደው ሻምፒዮና ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው በ <62 ኪሎ ግራም ሴት የደቡብ ክልሏ ሶስና ዳምጠው የአዲስ አበባዋን ቤተልሄም ዘውዴ አሸንፋ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ተጋጣሚዋ ቤተልሄም የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በ<62 ኪሎ ግራም ሴት በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት የኦሮሚያዋ አያት ጊዲ እና የድሬዳዋዋ ዮርዳኖስ ጥላሁን የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
በ<67 ኪሎ ግራም ሴት የኦሮሚያ ክልሏ ደሚ ሜኤሶ የደቡብ ክልሏን አይኔ አሰፋን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ አይኔ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በዚሁ የክብደት ዘርፍ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች የተሸነፉት የቤኒሻንጉል ጉምዟ ቅድስት አወቀ እና የአዲስ አበባዋ መሪማ ኑሪ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።
በ<68 ኪሎ ግራም ወንድ የደቡብ ክልሉ ሲያንሰው ዘኪ የኦሮሚያውን ሄኖክ ግርማን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሲሆን ተጋጣሚው ሄኖክ ግርማ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
በ<68 ኪሎ ግራም ወንድ የግማሽ ፍጻሜ ተሸናፊዎቹ የአዲስ አበባው አብዱልፈታ ሰፋ እና የአማራ ክልሉ አዲስ ተክለስላሴ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
ከአምስት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳሮች በወንድ 35 በሴት 31 በአጠቃላይ 66 ተወዳዳሪዎች በሻምፒዮናው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በወንዶች ከ<54 እስከ <80 ኪሎ ግራም፣ በሴቶች ከ<46 እስከ <67 ኪሎ ግራም ሻምፒዮናው የሚካሄድባቸው የውድድር ዘርፎች ናቸው።
የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ክልሎች በፋይናንስ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት በሻምፒዮናው ላይ አለመሳተፋቸውን ከኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ የሻምፒዮናው ዋና አላማ እንደሆነም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።
- < ምልክት የገባው በታች የሚለውን ለመወከል ነው።