አፋርና ኦሮሞ የጋራ እሴቶችን የሚጋሩ ህዝቦች መሆናቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አፋርና ኦሮሞ የጋራ እሴቶችን የሚጋሩ ህዝቦች መሆናቸው ተገለጸ
አዳማ ግንቦት 16/2011ዓ.ም አፋርና ኦሮሞ በቋንቋ ፣ ባህልና ኃይማኖታዊ ታሪክ የሚጋሩና በደም የተሳሰሩ ህዝቦች መሆናቸውን የኦሮሚያና አፋር ክልላዊ መንግስታት አስታወቁ።
በአዳማ እየተካሄደ ባለው የሁለቱ ህዝቦች የግንኙነት ኮንፍረንስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት በሁለቱ ህዝቦች መካከል አንድም ቀን ችግር ተፈጥሮ አያውቅም።
" በአብሮነትና መቻቻል በአንድነት የኖሩ ናቸው" ያሉት አቶ ሽመልስ በቋንቋ ፣ ባህልና ኃይማኖታዊ ታሪክ የሚጋሩ ህዝቦች እንደሆኑም አመላክተዋል።
የአፋር ክልል የሀገሪቱ የመውጫና መግቢያ በር መሆኑን አመልክተው “ ሁለቱን ህዝቦች በልማት ማስተሳሰር ይጠበቅብናል “ ሲሉ ገልጸዋል።
በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የጋራ ልማትን ለመዘርጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አፋር ፣ሶማሌና ኦሮሞ በምስራቅ አፍሪካ አጎራባች ሀገራት ጭምር በስፋት የሚኖሩ በመሆኑ የጋራ ትስስርና ግኝኑነት ማጠናከር ሁሉን አቀፍ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ሽመልስ አስረድተዋል።
ፅንፈኝነትን ለማስቀረት ብሎም ብዙሃኑን የምትመስል ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በመደገፍ የክልሉ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አስታወቀዋል።
“ወንድማማችነትና አንድነትን ከሁሉም ህዝቦች ጋር በማጠናከር በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር እናደርሳለን” ብለዋል።
የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው " የኦሮሞና አፋር ህዝቦች በደም የተሳሰሩ አንድ ቤተሰብ ናቸው" ሲሉ አስታውቀዋል።
አፋር ከኦሮሞ ጋር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን በማጠናከር ዛሬ ላይ መድረሳቸውን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ “አዳማ የመጣነው ተጋጭተን ለመታረቅ ሳይሆን የነበረንን አብሮነትና አንድነትን በመደጋገፍ ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ነው “ብለዋል።
ኦሮሚያ ከተረበሸ አፋር ሰላም እንደማያገኝ ገልጸው የሁለቱም ክልሎች ፀጥታና ደህንነት ማረጋገጥ የሁላቸውም ኃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል።
አቶ አወል በሰው ኃይል ፣ በልማትና በምጣኔ ሀብት እድገት ተጋግዘው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ቀጥሎ ባለው ኮንፍረንስ ከሁለቱም ህዝቦች የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ ወጣቶችና ሴቶች እየተሳተፉ ነው።