በህገወጥ መንገድ ወደጅቡቲ ሊወጡ የነበሩ 28 ሰዎች ተያዙ

94

ግንቦት 15/2011 በአፋር ክልል በኩል በህገወጥ መንገድ ወደጅቡቲ ለመውጣት ሲሞክሩ የተገኙ 28 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ።

ሰዎቹን አሳፍሮ ወደ ጅቡቲ ለማሳለፍ የሞከረን አሽከርካሪም ከነመኪናው መያዙም ተመልክቷል።

በኮሚሽኑ የአቤቱታ መርማሪ ዋና ሳጅን ሳልህ ሲብላሌ አንደተናገሩት የአፋር ክልል ከአማራና ከትግራይ ክልሎች በህገወጥ መንገድ ለሚደረግ የሰዎች ዝውውር አንድ መውጫ በር ነው።

በዛሬው ዕለትም ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሃራ ከተማ የሰሌዳ ቁጥር 3-10363 አ.ማ የለጠፈ ዶልፊን ሚኒባስ መኪና 28 ሰዎችን አሳፍሮና ጨለማን ተገን አድርጎ ወደጅቡቲ ለማለፍ ሲሞክር መያዙን ገልጸዋል።

ተሽከርካሪው ጧት 12ሰአት አካባቢ በጸጥታ ኃይሎች ሊያዝ የቻለው በዱብቲ ወረዳ ሰርዶ ቀበሌ ውስጥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከተያዙት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ወጣቶች ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥም አራቱ ሴቶች መሆናቸውን ነው ዋና ሳጅን ሳልህ ያስረዱት።

አሽከርካሪውን ጨምሮ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙት ግለሰቦችን የክልሉ ፖሊስ ከሚሽን ለፌደራል ፖሊስ አሳልፎ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ዛሬ የተያዙትን ጨምሮ በተያዘው በጀት አስካሁን ድረስ ከአማራና ከትግራይ ክልል ተነስተው በህገወጥ መንገድ ወደጅቡቲ ለመውጣት የሞከሩ 1ሺህ 78 ሰዎች በክልሉ ጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጉን ዋና ሳጅን ሳልህ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም