የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ተጀመረ
ግንቦት 15/2011 የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የወጣት ማዕከል ተጀመረ
ዛሬ በሻምፒዮናው የመክፈቻ ቀን ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ተደርገዋል።
ከአምስት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳሮች በወንድ 35 በሴት 31 በአጠቃላይ 66 ተወዳዳሪዎች በሻምፒዮናው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በወንዶች ከ<54 እስከ <80 ኪሎ ግራም፣ በሴቶች ከ<46 እስከ <67 ኪሎ ግራም ሻምፒዮናው የሚካሄድባቸው የውድድር ዘርፎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት አስፋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሻምፒዮናው ዋና ዓላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ነው።
ከሻምፒዮናው የተመረጡ ስፖርተኞች በወርልድ ቴኳንዶ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው በቀጣዩ ሳምንት ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩም ጠቁመዋል።
ከመላው አፍሪካ ጨዋታ በተጨማሪ ተወዳዳሪዎቹ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጣር በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሎምፒክ ውድድር በሚካሄዱ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
የውድድር አማራጮችን ከማስፋትና ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት አንጻር ሻምፒዮናው የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል።
በሻምፒዮናው ላይ ያልተሳተፉት የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ክልሎች በፋይናንስ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት እንደማይሳተፉ ለፌዴሬሽኑ ማሳወቃቸውን አቶ ዳዊት ገልጸዋል።
በየሁለት ዓመት የሚካሄደውን ሻምፒዮና በየዓመቱ ለማካሄድ ፌዴሬሽኑ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፍሰሀ ገብረሚካኤል በበኩላቸው ሻምፒዮናው በክልል የወርልድ ቴኮንዶ ስፖርትን ለማስፋፋትና ልምድ ለመቅሰም ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በኦሮሚያ ክልል እንዲያድግ ቁሳቁሶችን በመግዛት የወርልድ ቴኳንዶ ቡድኖችን በማቋቋምና በማገዝ እና የውድድር አማራጮች እንዲሰፉ በማድረግ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በ2012 ዓ.ም የወርልድ ቴኳንዶ ቡድኖችን ወደ ክለብ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።
ሻምፒዮናው ፍጹም ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት እንደተደረገ የገለጹት አቶ ፍሰሃ ተወዳዳሪዎች ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ ውድድሮችን እንዲያካሂዱም አሳስበዋል።
ዛሬ በሻምፒዮናው የመክፈቻ ቀን ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን በሴቶች <53 ኪሎ ግራም የደቡብ ክልሏ ተወዳዳሪ ይፍቱስራ ኤርሚያስ የአማራ ክልሏን ፍሬህይወት ታደሰን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ስታገኝ ተጋጣሚዋ ፍሬህይወት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በ<53 ኪሎ ግራም ሴቶች በግማሽ ፍጻሜው ጨዋታ የተሸነፉት የአዲስ አበባዋ ዮርዳኖስ ባባ እና የኦሮሚያ ክልሏ ቤተልሄም ለገሰ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል።
በ<57 ኪሎ ግራም ሴቶች የደቡብ ክልሏ ዘላለም ቡጭማየሁ የኦሮሚያዋን ቤተልሄም ብርሃኑን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሲሆን ቤተልሄም የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በ<57 ኪሎ ግራም ሴቶች በግማሽ ፍጻሜው የተሸነፉት የአማራ ክልሏ ረድኤት ጌታቸውና የአዲስ አበባዋ ዘውድነሽ በረከት የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ናቸው።
በ<54 ኪሎ ግራም ወንዶች የኦሮሚያው ፍጹም ዘውዴ የአዲስ አበባውን አቤኔዘር ሙሉጌታን አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ አቤነዘር የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።
በ<54 ኪሎ ግራም ወንዶች የግማሽ ፍጻሜ ተሸናፊዎቹ የአማራ ክልሉ ዘካሪያስ አዳነ እና የደቡብ ክልሉ ኢሳ ሱሌማን የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል።
በወርልድ ቴኳንዶ የውድድር ደንብ መሠረት በግማሽ ፍጻሜ ውድድር የተሸነፉት ሁለቱም ተወዳዳሪዎች የነሐስ ሜዳሊያ ያገኛሉ።
የፍጻሜ ውድድሮቹ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየባቸውና የተመልካቹን ትኩረት የሳቡ ነበሩ።
ሻምፒዮናው ነገም ሲቀጥል በወንዶች < 68 እና <80 ኪሎ ግራም በሴቶች <62 እና <67 ኪሎ ግራም የፍጻሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።