አምራች ኃይሉ ለአልኮል መጠጥ ያለውን ተጋላጭነትና የመጠጥን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኃይሉ ለአልኮል መጠጥ ያለውን ተጋላጭነትና የመጠጥን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ
ግንቦት 15/2011 በኢትዮጵያ አምራቹ ኃይሉ ለአልኮል መጠጥ ያለውን ተጋላጭነትና የመጠጥን ተጽዕኖ ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመተባበር በአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ላይ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች በቢሾፍቱ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
የኢትዮያ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኬረዲን ረዲ እንደገለጹት የአልኮል መጠጥ አጠቃቀምና የአምራቹን ኃይል የመጠጥ ተጋላጭነት ለመቀነስ መንግስት አዲስ አዋጆችና መመሪያዎችን በማውጣት የቁጥጥር ስርአት ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
ወጣቱን ለጤና፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረጉት ካሉ ጉዳዮች መካከል የአልኮል መጠጥ አንዱ መሆኑን አስታውሰው “የችግሩን አሳሳቢነት ለመቀነስ አዋጅ ቁጥር 1112/2011 በማዘጋጀት ወደ ሥራ ተገብቷል” ብለዋል።
ከአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ዝግጅት፣ ስርጭትና ማስነገር ጀምሮ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ህግ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ አዘጋጆች፣ አሰራጮችና አስነጋሪዎች ስለአዋጁ በቂ ግንዛቤ ኑሯቸው ርብርብ እንዲያድረጉ ለማስቻል ጭምር ታስቦ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው መድረኩ አዋጁን ተከትሎ ለተዘጋጀው መመሪያ ተፈፃሚነት በህግ ድንጋጌዎች ዙሪያ በዘረፉ ተዋናይ የሆኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
በአልኮል መጠጥና በምግብ ማስታወቂያዎች ላይ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ሙያተኞች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው ለአዋጁ ውጤታማነት መረባረብ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
“አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ከመስጠት ባለፈ በህዝባዊ ተቋማት፣ ማዕከላትና ቦታዎች ላይ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ ማስነገርም ሆነ ስፖንሰር ማድረግ ፣ በአይነትና በገንዘብ መደገፍ እንደማይቻል ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል” ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ዝርዝር የአዋጁን ይዘት ያቀረቡት አቶ ደረጄ ሽመልስ በበኩላቸው እንደገለጹት በቲሸርት፣ ቢልቦርድ ፣ ቁልፍና በሌሎች የማስታወቂያ ቁሳቁሶች የተለጠፉ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች መመሪያው ተፈፃሚ መሆን ከጀመረበት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማስንሳት ይኖርባቸዋል።
በአልኮል ምርታቸው ላይም የጤና ማስጠንቀቂያ፣ የአልኮል ይዘት መጠን፣ ስለአቀማመጥና ተያያዥ መረጃዎችን በምርቱ ማሸጊያ በግልጽ በሚታይበት ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
እንደ አቶ ደረጄ ገለጻ በዓለም ላይ በአልኮል መጠጥና በሲጋራ ጢስ ምክንያት 10 ሚሊዮን ዜጎች በየዓመቱ ለሞት ይዳረጋሉ።