ቀጥታ፡

ኢዜማ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ግንቦት 15/2011 የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ- ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ይፋ አደረገ።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ 20 አባላት ያሉትን የብሄራዊ ሥራ  አስፈጻሚ  ኮሚቴ አባላት ይፋ አድርገዋል።

የስራ አስፈፃሚ አባላቱ ምርጫም የትምህርት ዝግጅታቸውን፣ የፓርቲውን አላማ  መረዳትን፣ የፖለቲካ ተሳትፎና ብቃታቸውን እንዲሁም ልምዳቸውን መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀመንበሩ ስለ እያንዳንዱ ስራ አስፈፃሚ አባላት ግለ ስብዕና ማብራሪያ  በመስጠት ለመገናኛ ብዙሃን አስተዋውቀዋል።

የአገሪቷን ህግና የፓርቲውን ስነ ምግባር ጠብቀው እንደሚሰሩም ያላቸውን  እምነት  ገልጸዋል።

የስራ አስፈፃሚ አባላቱም በእለቱ ቃለ መሃላ በመፈፀም ሃላፊነታቸውን  በታማኝነት  ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።

ኢዜማ ያልተማከለ አስተዳደር (ፌዴራላዊ) ሥርዓትን መከተልን ምርጫው  ያደረገ  ፓርቲ ሲሆን ከፍተኛው የመንግሥት ሃላፊነት በሕዝብ ቀጥታ ምርጫ በሚመረጥ  ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓት ይከተላል።

ፓርቲው ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ ሲቋቋም ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋን  በድርጅት  መሪነት፣ አቶ አንዷለም አራጌን በምክትልነት፣ አቶ የሺዋስ አሰፋን  የፓርቲው  ሊቀ መንበር፣ ዶክተር ጫኔ ከበደን ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር አድረጎ መሰየሙ  ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም