ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ ብድር ወስደው ወደሥራ የገቡ ሴቶች ለውጥ ማምጣታቸውን ገለጹ

ግንቦት 15/2011 በጎንደር ከተማ በተመቻቸላቸው የገንዘብ ብድር በአነስተኛ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ሴቶች በኑሯቸው ላይ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ተናገሩ። 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች መምሪያ በበኩሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተሰራው ሥራ 1ሺህ 400 ሴቶች የገንዘብ ብድር እንዲያገኙ መደረጉን አስታውቋል፡፡

የብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ለኢዜአ እንደተናገሩት ያገኙት የገንዘብ ብድር ሰርተው የራሳቸውን ገቢ ለማግኘትና ኑሯቸውን ለማሻሻል አግዟቸዋል፡፡

በባልትና ውጤት ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ ዘውዲቱ ተሾመ እንዳሉት ባለፈው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም በተሰጣቸው የ15 ሺህ ብር ብድር ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡

"ከዚህ ቀደም መስሪያ ብር ስለሌለኝ የእለት ወጪን ለመሸፈንና ልጆቼን ለማስተማር እቸገር ነበር " ያሉት ወይዘሮዋ በአሁኑ ወቅት የራሳቸው ገቢ ስላላቸው ችግራቸው መቃለሉን ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛዋ ተጠቃሚ ወይዘሪት አያልነሽ አስናቀው በበኩሏ 30 ሺህ ብር በመበደር በአነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ መሰማራቷን  ገልፃለች፡፡

በንግድ ሥራ ከተሰማራች ወዲህም ከእጅ ወደ አፍ የነበረው ኑሮዋን በማሻሻል ጥሪት ወደ ማፍራት ደረጃ መድረሷን ተናግራለች፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ሴቶች መምሪያ በኩል የተሰጣቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትም ለውጤታማነት እንዳገዛት ጠቁማለች።

በወሰደችው የገንዘብ ብድር የሴቶች ሳሎን ቤት ከፍታ እየሰራች መሆኗን የተናገረችው ደግሞ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት የተመረቀችው ወጣት ማኪባ አፈወርቅ ናት።

"ከብድር ባገኘሁት 20ሺህ ብር እና ከቤተሰቦቼ በተደረገልኝ እገዛ ወደ ሥራ ገብቼ ከራሴ አልፌ ለሌላ አንዲት ሴት ስራ ፈጥሪያለሁ" ያለችው ወጣቷ በእዚህም ብድሯን መመለስ መጀመሯን ገልጻለች።   

"በብድር የሚሰጠው አነስተኛ ብር ነው፤ አይጠቅመንም" በሚል ያልተገባ ምክንያት ወደ ሥራ የማይገቡ ሴቶች ባላቸው የገንዘብ መጠን  ስራ በመፍጠር ኑሯቸውን እንዲለውጡ መክራለች፡፡

በጎንደር ከተማ ሴቶች መምሪያ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማካተት ቡድን መሪ ወይዘሮ ሰላማዊት ቦጋለ በበኩላቸው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ የመስሪያ ብድር እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

ለዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለአንድ ሺህ 400 ሴቶች ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ከአማራ ብድርና ቁጠባ ጋር በመነጋገር 37 ሚሊዮን ብር እንዲያገኙ መደረጉን በማሳያነት ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት እንዳሉት ለሴቶች ብድር ከመስጠት ባለፈ ገንዘቡን በአግባቡ ሥራ ላይ አውለው ብድራቸውን እንዲመልሱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋል፡፡

በዚህም በከተማው በስድስት ክፍለ ከተሞች በተደረገ ተከታታይ ድጋፍ ወደ ስራ የገቡት ሴቶች ቁጠባ መጀመራቸውንና በእዚህም ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠብ እንደቻሉ መረጋገጡን ወይዘሮ ሰላማዊት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ሴቶችን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲላቀቁ ለማድረግ የሚያስችሉ እቅዶች ተይዘው እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም