ቀጥታ፡

በየመን ባህር ዳርቻ በሰጠመችዋ ጀልባ በትንሹ 46 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጡ

ግንቦት 30/2010 መነሻቸውን ከሶማሊያ አድርገው በአንዲት ጀልባ ወደ የመን ለመሻገር ከሞከሩት 100 ኢትዮጵያውያን ውስጥ ቢያንስ 46ቱ መስጠማቸውን  ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ማህበር አስታውቋል፡፡ በጀልባዋ ከተሳፈሩት ውስጥ 16ቱ አሁንም ድረስ የደረሱበት አለመታወቁም ተገልጿል፡፡ ማህበሩ እንዳስታወቀው  ስደተኞቹ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ አማካኝነት ከሶማሊያ ወደብ ቦሳሶ ተነስተው ወደ የመን ለመሻር የሚሞክሩ ነበሩ፡፡ በኤደን ባህረ ሰላጤ ትናንት ጠዋት በሰጠመችዋ ጀልባ ህይወታቸውን ካጡት መካከል 37ቱ ወንዶች ሲሆኑ ዘጠኙ ሴቶች መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በጀልባዋ የተሳፈሩ ስደተኞች የአደጋ ጊዜ ጃኬቶችን አለመጠቀማቸው አደጋውን እንዳባባሰውም ነው የተገለጸው፡፡ የማህበሩ የክዋኔና ድንገተኛ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሞሀመድ አብዲክ እንዳሉት  በየወሩ ከ7 ሺህ በላይ ስደተኞች በዚህ መስመር ወደ የመን ይሻገራሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ 100 ሺህ ስደተኞች ይህን የጉዞ መስመር እንደተጠቀሙበት ገልጸው በዚህ መስመር የሚደረገው ጉዞ አደገኛና ዘግናኝ በመሆኑ ሊቆም እንምደሚገባው  አሳስበዋል፡፡ የመን ለምስራቅ አፍሪካ ካላት ቅርበት አንጻር  ላለፉት አስርት ዓመታት በርካታ የቀጠናው ስደተኞች የመንን ጨምሮ ወደ ሌሎች የባህረሰላጤው ሀገራትና አውሮፓም ጭምር ለመሸጋገር ወደ የመን ተጉዘዋል፡፡ የመን በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመስና  በከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ብትሆንም በርካታ ስደተኞች ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውን አላቋረጡም፡፡ በየመንና ሌሎች የባህረሰለጤው ሀገራት ስራ ፍለጋ ወደ የመን በመጓዝ ላይ ከነበሩ 100 ስደተኞች ውስጥ 17ቱ ሴቶች እንደነበሩ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም