ቀጥታ፡

የሃይማኖት አባቶች የሽምግልና ስራቸውን ያለማቋረጥ እንዲያከናውኑ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2011  የሃይማኖት አባቶች የሽምግልና ስራቸውን በማጠናከር ቂም በቀል እየከሰመ ይቅርታ አንዲያብብ መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

ፓትሪያሪክ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሃይማኖት አባቶች በየሃገረ ስብከታቸው በመገኘት ጸሎተ ምህላን በመምራትና ትምህርት በመስጠት ቂም በቀል እንዲከስም ይቅርታ እንዲያብብ ያለማቋረጥ የሽምግልና ስራን መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ የህዝብ እረኛ እንደመሆኑ አባቶች ከአገረ ስብከታቸውና ከህዝባቸው ሳይለዩ ህዝብን ሊመክሩ፣ ሊያስተምሩ፣ ሊያስታርቁና ሊያጽናኑ ይገባልም ብለዋል።

የእምነቱ ተከታዮች የአባቶችን ትምህርት፣ ምክርና ተግሳጽ ተቀብሎ በመፈጸም ለኢትዮጵያ ሰላም እንዲተጉም መክረዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለግጭትና ለመለያየት በር ከሚከፍቱ ተግባራትና ቅስቀሳዎች ተቆጥበው የአገር ሰላምና አንድነትን የጋራ አጀንዳ አንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ችግሮችን በውይይት ብቻ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ፣ ሃይለ ቃል መጠቀምንና ስም ማጥፋትን እንዲያቆሙም ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን በተደጋጋሚ ምህላና ጸሎት እንዲደረግ፣ የሰላምና የአንድነት አስተምሮ በስፋት እንዲሰጥ፣ ይቅር የመባባል ልምድ እንዲሰርጽ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች በትኩረት እንዲሰሩ ቀደም ሲል መወሰኑን አስታውሰዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን ህንጻዎችን ለማስመለስ ለአመታት በአቤቱታ የተደከመበትን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲመለስ በማድረጋቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በመሰብሰብ ስለ ቤተክርስቲያን፣ የአገር ሰላምና አንድነት በመምከር ውሳኔዎችን ያሳልፋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም