ቀጥታ፡

የአለም ሩጫ ቀንን የሚያስብ የጎዳና ላይ ውድድር በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 ሶስተኛውን የአለም የሩጫ ቀንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የ1 ነጥብ 6 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ተካሄደ። መነሻውንና መድረሻውን ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ያደረገው ውድድር የአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከከተማ አስተዳደሮችና የውድድር አዘጋጆች ጋር በትብብር ያዘጋጀው ነው። ውድድሩ በ23 አገሮች በሚገኙ 24 ከተሞች በተመሳሳይ ሰአት ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ናት። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ እንደገለጸው ውድድሩ አትሌቲክስ ህብረተሰቡን የሚያስተሳስርና የሚያቀራርብ ነው። በተጨማሪም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብሏል። በአለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር ኢትዮጵያ ውድድሩ እንዲካሄድባት መመረጧ አገሪቱ በአትሌቲክስ ስፖርት ያላትን ተቀባይነት የሚያሳይ መሆኑንም ገልጿል። ውድድሩ በተመሳሳይ ሰአት ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል ቶኪዮ፤ ጆሃንስበርግ፤ ባንኮክን ጨምሮ ሌሎች 24 ከተሞች ላይ ተካሂዷል። ውድድሩ "ሩጫ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ መሆን አለበት" የሚለው የአለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር መርህ አካል ነው።   በውድድሩ 200 የሚጠጉ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ለውድድሩ አሸናፊዎች የብር፤ የወርቅና ነሃስ ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።   በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎን ጨምሮ ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም