''ዘረኝነት ይብቃ '' በሚል መሪ ሀሳብ የቦክስ ውድድር ሊካሄድ ነው

73

አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011 በአገሪቱ አደጋ እየሆነ የመጣውን ዘረኝነት ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት የማገዝ ዓላማ ያለውና ''ዘረኝት ይብቃ '' በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የቦክስ ውድድር በአዲስ አበባ ሊካሄድ መሆኑን የከተማው ቦክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። 

የአዲስ አበባ ቦክስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

በዚሁ ወቅት የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አርአያ ብርሃኔ እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ ዘረኝነትን የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ መልዕከቶች ለማስተላለፍና ጎን ለጎን ስፖርቱን ማስፋፋት ነው።

ዝግጅቱ ክለቦችን በስፖርቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም ያገዛል ብለዋል።

ውድድሩ የአዲስ አበባ ፖሊስን ጨምሮ ሰባት ክለቦች ይካፈላሉ ተብሏል።

ከሰባቱ ተሳታፊዎች መካከል ስድስቱ ከአዲስ አበባ ከተማ የተወከሉ ሲሆን  የድሬድዋ ከነማ ቦክስ ክለብም የውድድሩ አካል ነው።  

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ተወካይ አቶ በኋይሉ በቀለ ፌዴሬሽኑ ይህን በአይነቱ ለየት ያለ ውድድር ለማዘጋጀት መነሳሳቱ የሚያስመስግነው ተግባር ነው ብለዋል።

"ስፖርቱን ለአንድንትና ለሰላም በማዋል በኩል ብዙ ያልተከናወኑ ተግባራት አሉ፤ በዚህም የተነሳ ስፖርት ውጭ ያሉ ዜጎችን ሊያቀራርብ ቀርቶ በስፖርቱ ውስጥ ያሉትን እንኳ ሲከፋፍል ይታያል" ሲሉ ተናግረዋል።

ውድድሩ ይህን  አስተሳሰብ ሰብሮ በመግባት በስፖርቱ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለዜጎች መፈናቀል የሚያስከትሉትን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ሁለንተናዊ መስተጋብሮች  ውስጥ ያለው ችግር  ለመፍታት የራሱን ጡብ ማስቀመጥ ዓላማው እንደሆነ አስረድተዋል።

ውድድሩ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሁለገብ ስታዴየም የሚጀመር ሲሆን ፍጻሜው ደግሞ ከአራት  ቀናት በኋላ  በመስቀል አደባባይ ይሆናል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም