አራት የጋምቤላ ክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
አራት የጋምቤላ ክልል ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ
ግንቦት 13/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘንድሮ አራት የጋምቤላ ክልል ከተሞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ።
በክልሉ የመብራት አገልገሎቱን ተደራሽ ለማደረግ የተጀመሩ ሥራዎች ቢበረታቱም አሁንም አገልገሎቱ ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት የጋምቤላ ሪጅን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቢቂላ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በክልሉ የ24 ስዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከታቀዱት ስድስት የክልሉ ከተሞች መካከል በአሁኑ ወቅት አራቱ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።
እንደ አቶ በቂላ ገለጻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት የክልሉ ከተሞች መካከል የፉኝዶ፣ የኝንኛንግ፣ የቢል ዋንኬና አዴንገ የዞን፣ የወረዳና የገጠር ከተሞች ይገኙበታል።
ቀሪዎቹ የጆር ወረዳና የቾቦኪር ከተሞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራው በሂደት ላይ እንደሆነና እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ከተሞቹ ደረጃ ቅድሚያ በመስጠት ሁሉንም የክልሉ አካባቢዎች በኃይድሮና በሶላር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።
“በተጨማሪም ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ምክንያቶች የሚከሰተውን የኃይል እጥረትና መቆራረጥ ችግር ለማቃለል ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል አቶ በቂላ።
በተለይም ኃይል ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶዎች በእርጅና ምክንያት እየወደቁ የሚከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ለማስቀረት ያረጁትን በኮንክሪት ምሰሶ የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የኑዌር ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሙድ ቶክ በበኩላቸው “የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመብራት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸው ስራዎች መልካም ቢሆኑም ብዙ ቀሪ ሥራዎች አሉ” ብለዋል።
በዞኑ ከሚገኙት አምስት የወረዳ ከተሞች መካከል እስካሁን በቅርቡ የአገልገሎቱ ተጠቀሚ የሆነውን የኝንኛንግ ከተማን ጨምሮ ሁለት ከተሞች ብቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“በቀጣይም አገልግሎቱን ወደ ሌሎች የወረዳ ከተሞች ተደራሻ ለማድረግ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት ከተሞች መካከል የኝንኛንግ ከተማ ነዋሪ አቶ ፓም ጋትዊች በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በከተማው የኤክትሪክ አገልገሎት ባለመኖሩ ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዘንድሮ ዓመት አገልግሎቱን በማግኘታቸው መደሰታቸውን የገለጹት አቶ ፖም ፣ ብዙ የከተማው ነዋሪዎችመብራት በመጠቀም የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ማከናወን መጀመራቸውን አስረድተዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ ወደ ሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
ከአሁን በፊት የመብራት አገልገሎትን በተወሰነ ጊዜ ብቻ ስለሚያገኙ ሲቸገሩ እንደነበር የገለጹት ደግሞ የፉኝዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ኑረዲን እንድሪስ ናቸው።
በቅርቡ ከተማዋ የ24 ስዓት የመብራት አገልገሎት ተጠቃሚ በመሆኗ ቀደም ሲል የነበረው ችግር መፈታቱንና የተሻለ አገልገሎት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጎግ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪ አቶ ታታ ኡዋር በበኩላቸው ቀደም ሲል በወረዳው የፍኝዶ ከተማ የ24 ስዓት የመብራት አገልግሎት ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ለንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በቅርቡ ከተማዋ የ24 ስዓት የመብራት አገልገሎት ተጠቃሚ በመሆኗ ችግሩ መቃለሉን ተናግረዋል፡፡