የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሠላምና አብሮነት የሚያደርገውን አስተዋፆ እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለሠላምና አብሮነት የሚያደርገውን አስተዋፆ እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ግንቦት 13/2011 የሠላም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለአገር ሰላም የሚያደርገወን አስተዋፆ እንዲያጠናክር ጥሪ አቀረበ።
የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ነባር አመራሮችን በመሸኘት አዳዲስ አመራርና አባላትን አቀባበል ሥነ ስርዓት አካሂዷል።
ላለፉት ስምንት ዓመታት ጉባኤውን በጠቅላይ ጸሐፊነት ሲመሩ የነበሩት መጋቢ ሀዲስ ዘሪሁን ደጉ በሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተተክተዋል።
በሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ጉባኤው ባለፉት ዓመታት በአገሪቷ ዕርቅ፣ ሠላምና አንድነት እንዲመጣ የራሱን አወንታዊ አሻራ ሲያሳርፍ ቆይቷል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቷ የተከሰተው አለመረጋጋት ኃይማኖታዊ አጀንዳ እንዳይሆን የተሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቀጣይም ለአገሪቷ ሠላምና ዕድገት መስራት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
''የጉባኤው የቀድሞ አመራሮች በአገሪቷ አንድነትና ፍቅር እንዲጎለብት ሚናቸውን ተወጥተዋል'' ያሉት ወይዘሮ አልማዝ ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ሠላም እንዲጠበቅ ጉባኤውን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የጉባኤው ሰብሳቢ አቡነ ጎርጎሪዮስ በበኩላቸው ''አሁን ችግሮች እየገጠሙን ነው፤ ከምን ግዜውም በላይ በጋራ የምንሰራበት ጊዜ ነው'' ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚታየው የሠላም እጦት መፍትሄ እንዲያገኝ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።
የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አሁን ለሚታዩ ችግሮች ዋናው መንስኤው የግብረገብነትና ሥነ ምግባር መጓደል መሆኑን ይናገራሉ።
"በሰዎች መካከል መተዛዘን፣ ደግነትና መረዳዳት ሊኖር ያስፈልጋል፤ ጨለማን ብርሃን እንጂ ጨለማ አያሸንፈውም" በማለት ገልጸዋል።
ቤተ እምነቶች ሥነ-ምግባር ላይ አበክረው እንዲሰሩ በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤን ከፖለቲካ ተጽዕኖ ማላቀቅ ትልቁ አጀንዳ እንደሚሆንም ነው ጠቅላይ ጸሐፊው ያመለከቱት።
በአገሪቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የዜጎች መፈናቀልና ስደት እንዲያበቃ ተቋሙ ሚናውን እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።
ቀደም ሲለ ጉባኤውን በአመራርነት ላገለገሉት መጋቢ ዘሪሁን ደጉና ለቀድሞው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጠቅላይ ምክር ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ አሚን የዕውቅና እና ሽልማት ሥነ-ስርዓት ተካሂዷል።