ቀጥታ፡

ትራይባስ በሪችቴክ ኢትዮጵያ የወንድ ሙሉ ሱፍ ልብሶችን ዛሬ ወደ አሜሪካ መላክ ይጀምራል

ግንቦት 13/2011 በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ"ትራይባስ በሪችቴክ ኢትዮጵያ" ደረጃቸውን የጠበቁ የወንድ ሙሉ ሱፍ ልብሶችን ዛሬ ወደ አሜሪካ መላክ እንደሚጀምር የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ሙሉጌታ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ኩባንያው በአሜሪካና በቻይና ባለሀብቶች ተቋቁሞ ከመስከረም  2011ዓ.ም ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል።

ባለፉት ወራትም ሠራተኛ ቀጥሮ ሲያሰልጥን፣ አስፈላጊ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባና ለማምረት አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቶ በአሁኑ ወቅት ወደ ምርት ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

“እስካሁን ያመረታቸውን ከ4 ሺህ በላይ ደረጃቸውን የጠበቁ  የወንድ ሙሉ ሱፍ ልብሶችን ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካን ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቋል” ብለዋል፡፡

ኩባንያው ዛሬ የሚልካቸው የሱፍ ልብሶች 60 ሺህ የሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

በቀጣይም በየሳምንቱ አንድ ኮንቴይነር ሱፍ ለመላክ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ገልፀዋል፡፡

ምርቱን በይፋ መለካ መጀመሩን ለማብሰር ዛሬ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና  የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮችና ተጋባዥ ባለድርሻ አካላት በኮምፖልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

"የትራይባስ በሪችቴክ ኢትዮጵያ" ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ ሠራተኞችን በቋሚነት ቀጥሮ በማሰራት ላይ ይገኛል፡፡

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ ላይ ከሚገኙ አራት ኩባንያዎች ሦስቱ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት እየላኩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም