የዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ የበኩላችንን እንወጣለን - የትግራይ ክልል ፍትህ አካላት

61
መቀሌ ግንቦት 29/2010 የዜጎች ህገ-መንግስታዊ መብቶች ሳይሽራረፉ እንዲከበሩ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የትግራይ ክልል የፍትህ አካላት አስታወቁ፡፡ የፍትህ አካላቱ ይህን ያስታወቁት በህገ መንግስት ፅንሰ ሃሳብ አተረጓጎምና ተዛማጅ  ጉዳዮች ዙሪያ የፌዴሬሸን ምክር ቤት በክልሉ ለሚገኙ የፍትህ አካላትና ከፍተኛ የሰራ ኃላፊዎች ያዘጋጀው የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በመቀሌ ከተማ በተካሄደበት ወቅት ነው። የዜጎችን መብት አስመልክቶ በህገ መንግስቱ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ላይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሐጎስ  እንዳሉት የህግ የባላይነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በፍትህ ስርዓቱና ዳኝነት ዙሪያ ዜጎች እርካታ ማግኘት ሲችሉ ነው፡፡ ሰለሆነም በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የሰራ ኃላፊዎችና የፍትህ አካላት የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለህግ ተገዢ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠርም በየትምህርት ተቋማቱ አዲሱን ትውልድ ማሰተማሪ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡ የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አስፋ በበኩላቸው “ህገ መንግስት ፅንሰ ሐሳብና አተረጓጎም ላይ የተዘጋጀው የውይይት መድረክ በየደረጃው በሚገኙ አመራሮችና የፍትህ አካላት ያለውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ይረዳል'' ብለዋል። የፌዴሬሸን ምክር ቤት የህገ መንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እሸቱ ደሴ እንደገለፁት የምክክር መድረኩ የአቅም ውስንነትና የቀናነት ችግርን ለማስተካከል ያግዛል። ''በህግ አትረጓጎም ክፍተት የህዝቦችን ጥቅም ይጎዳል''  ያሉት አቶ እሸቱ ለህብረተሰቡ ፍትሃዊ ውሳኔ ለመስጠት በሙያተኞች ዘንድ ያለውን የአቅም ውስንነት ችግር የመፍታት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም