ህብረተሰቡ የቅዱስ ያሬድ መገለጫ የሆኑትን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ የቅዱስ ያሬድ መገለጫ የሆኑትን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ሊያጠናክር እንደሚገባ ተጠቆመ
ግንቦት 11/2011 ህብረተሰቡ እርስ በርስ መለያየትን ትቶ የቅዱስ ያሬድ መገለጫ የሆኑትን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ሊያጠናክር እንደሚገባ በአክሱም ከተማ በቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የታደሙ ተሳታፊዎች ተናገሩ።
የቅዱስ ያሬድ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአክሱም ከተማ የጎዳና ላይ ትዕይንት ተካሂዷል።
ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት ህብረተሰቡ መለያየትን ትቶ የቅዱስ ያሬድ መገለጫ የሆኑ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ሊያጠናክር ይገባል።
ከአዲስ አበባ ሀገረ ስበከት የመጡት ሊቀ ብርሃን ዮሐንስ መዝገቡ ቅዱስ ያሬድ ትልቅ ጸጋ የተሰጠውና ታሪክ የማይዘነጋው ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ትውፊትን ያበረከተ ሊቅ መሆኑን አስታውሰዋል።
የቅዱስ ያሬድ ስራዎች የኢትዮጵያውያን መለያ መሆናቸውን የተናገሩት ሊቀ ብርሃን ዮሐንስ ስራዎቹን ለዓለም የማስተዋወቁ ጉዳይ ከትውልዱ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ እርስ በርስ መለያየትን ትቶ የቅዱስ ያሬድ መገለጫ የሆኑ አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ሊያጠነክር እንደሚገባ መክረዋል።
ከድሬዳዋ ሃገረ ስብከት የመጡት ሊቀ ካህናት ቀለመወርቅ ሙሉ በበኩላቸው በጎዳና ትዕይንቱ ላይ ለበዓሉ ተሳታፊዎች አስተማሪ የሆኑ ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ሀገራዊ ስርአቶች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ቅዱስ ያሬድ መለያየትን፣ ክፋትንና ጠብን በማስወገድ ስለ ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር ያስተማረ የፍልስፍና እና የጥበብ ሊቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ሀገረ ስበከትን በመወከል በበዓሉ ላይ የታደሙት ሊቀ ህሩያን ቤዛኩሉ ሞላልኝ በበኩላቸው ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ ሊቃውንት የቅዱስ ያሬድ በዓልን በአንድነት ማክበራቸው እና መሰባሰባቸው የሚያስደስትና አንድነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
"ቅዱስ ያሬድ ከአክሱም በመነሳት የኢትዮጵያን ማንነት የገለጸ የዓለም ትልቅ ሀብት ነው" ያሉት ሊቀ ህሩያን ቤዛኩሉ፣ ክብረ በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ የሚያስደስት መሆኑን ገልጸዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ የቅዱስ ያሬድ የዜማና የቅኔ መሳሪያዎች፣ የግዕዝ ጽሑፎች፣ ሃይማኖታዊ ዝማሬና አቋቋም የሚያሳዩ ትእይንቶች በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ቀርበዋል።
በበዓሉ ላይ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የሀገረ ስብከት ተወካዮች፣ የቤተክርስትያን ሊቃውንትና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በተያያዘ ዜና የቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ ኃውልትን ለማሰራት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አባ መቃርዮስ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ኃለፎም፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ተስፋይ እና የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካሕሳይ በጋራ በመሆን የመሰረተ ደንጋዩን አስቀምጠዋል።
የመታሰቢያ ኃውልቱ በአንድ ባለሀብት በተመደበ 2 ሚሊዮን ብር በጀት የሚሰራ መሆኑም ለማወቅ ተችሏል።