ቀጥታ፡

ለአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ስኬት የበኩላችንን ለማበርከት ዝግጁ ነን - የፖለቲካ ፓርቲዎች

ግንቦት 10/2011 ለአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጾ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ።

ፕሮጀክቱ ከተማዋን ጽዱና ውብ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጡኑ ለማጠናከር የሚያግዝ በመሆኑ ህዝቡ ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፍ እንዲያደርግ  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ የኢትዮጵያ ዴሚክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲዎች ከተማዋን ጽዱና ውብ ለማድረግ ለተጀመረው  የወንዞች ዳርቻ ልማት ስኬት በተለያየ መንገድ አስተዋፅኦ በማድረክ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

የአዜማ ምክትል መሪ አቶ አንዷለም አራጌ፤  የአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረው ይህን ሁኔታ ለመቀየር በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አድንቀዋል።

የከተማዋ የፅዳት ጉዳይ በመንግስት ቁርጠኝነት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ህዝቡ የባለቤትነት ስሜት በመያዝ እንደመደበኛ ስራው ሊከውነው ይገባልም ብለዋል።

በከተማዋ የሚካሄደው የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይረው ፅኑ እምነት አለኝ ሲሉም አቶ አንዷለም ገልፀዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን ታፈሰ እና የኢትዮጵያ ዴሚክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ጎሹ ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ከተማዋን እንደ ስሟ ጽዱ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ተናግረዋል።

ከእንጦጦ እስከ አቃቂ የሚደርሰው የሸገር የወንዞች ዳርቻ ፕሮጀከት 56 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 29 ቢሊየን ብርም ተበጅቶለታል።

የፓርቲው መሪዎች እንዳሉት ከወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በፊት ሁሉም ሰው አካባቢውን ማጽዳት ከቻለ ከተማዋን መለውጥ ይቻላል።

በመጨረሻም የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከቆሻሻ የፀዳች ከተማ ትሆን ዘንድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ጥሪ አቅርበዋል ።

በመላው ኢትዮጵያ በነገው እለት ወርሃዊ የፅዳት ዘመቻ ይካሄዳል፤ በፅዳት ዘመቻውም  ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ መላው ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም