ኢትዮ- ኒፖን ቴክኒካል ኩባንያ ለተፈናቃይ ዜጎች የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ

76

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2011 ኢትዮ-ኒፖን ቴክኒካል ኩባንያ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን የሚሆን የ500 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገ።

የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንና ማሽኖችን ከውጭ አገር በማስመጣት ለአገር ወስጥ ገበያ በማቅረብና በቴክኒክ ድጋፍ ሥራ የተሰማራው ኩባንያው የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፉን ዛሬ ለብሄራዊ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን አስረክቧል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ዮሴፍ ለኢዜአ በሰጡት ቃል "በተለያዩ ችግሮች ምንክያት ከቤት ንብረታቸውና ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በገንዘብ፣ በምግብ፣ በአልባሳት እና በሌሎችም መንገዶች ድጋፍ በማድረግ ማስታወስ ያስፈልጋል።" ብለዋል። 

ኩባንያቸው ዛሬ የለገሰው የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍም የበኩሉን ለመወጣትና ሌሎችም በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን በሚችሉት ሁሉ እርዳታ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን የሃብት አስተዳደርና ፈንድ አሰባሰብ ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ ጊዜ በበኩላቸው፤  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ተፈናቃይ ዜጎች እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል ብለዋል። 

በተፈጥሮና በግጭት ምክንያቶች ተፈናቅለው የሚገኙት እነዚህ ዜጎችን ለማቋቋም 21 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

ይህን ችግር መንግስት ብቻውን ሊወጣ የሚችለው ባለመሆኑ አለም አቀፍ ማህበረሰብ፣ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ተቋማት እንድሁም ማንኛውም ህብረተሰብ ሃላፊነቱን በሚችለው መንገድ መወጣት አለበት ነው ያሉት።

የአገርን ችግር በጋራ የመካፈል ባህልን ማዳበር ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮ-ኒፖን ኩባንያ ያበረከተው የ500 ሺህ ብር አስተዋፅኦም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም