በጎባ ከተማ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በጎባ ከተማ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
ጎባ ግንቦት 10/2011 በጎባ ከተማ አለአግባብ የተያዙ የቀበሌ መኖሪያና የንግድ ቤቶችን በማስለቀቅ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች ለማስተላለፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ በከተማዋ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ “ በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን ለችግረኞች ለማስተላለፍ ግብረ ኃይል አቋቁሜ እየሰራሁ ነው “ብሏል፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳሉት ቤቶቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚኖሩ ግለሰቦች መሰጠት አለባቸው።
በከተማዋ የምስራቅ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከድር ሀሱ በከተማዋ ባለ ሦስት ወለል ሕንፃ መኖሪያ ቤት የገነቡ ግለሰቦች ቤታቸውን እያከራዩ በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩበት ሁኔታ መቀየር እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዙ መኖሪያ ቤቶች የከተማ አስተዳደሩ በማስለቀቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማስተላለፍ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት እንደሚደግፉም ተናግረዋል።
“መንግሥት ቤቶችን ለማይገባቸው ሰዎች የሚያስተላልፉ የቀበሌ አመራሮች ላይ ቁጥጥር ሊያደርግባቸው ይገባል “ያሉት ደግሞአቶ በቀለ ኃይሌ የተባሉት ነዋሪ ናቸው፡፡
“አስተዳደሩ አቅመ ደካሞችን የቤት ባለቤት ለማድረግ የሀገር ሽማግሌዎችና ገለልተኛ አካላትን በማሳተፍ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃተገቢናፍትሃዊነት በመሆኑ እንደግፈዋለን “ ብለዋል፡፡
አቶ በቀለ የከተማ አስተዳደሩ የተለቀቁ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች አቅመ ደካሞችንና ሥራ አጦችን ባማከለና ፍትሃዊነትን ባረጋገጠ መልኩ ለሚገባቸው ሰዎችመስጠት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
የጎባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አህመድ ሐጂ በበኩላቸው በከተማዋ የቀበሌና የንግድ ቤቶች በማይገባቸው ግለሰቦች አለአግባብ መያዛቸው የነዋሪዎቹ የረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንደነበር አስታውሷል፡፡
ቤቶቹን በማስለቀቅ ለችግረኞች ለማስተላለፍ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አመልክተዋል፡፡
“በሕገ ወጥ መልኩ ለዓመታት የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችን በማስለቀቅ መኖሪያ ቤት ለሌላቸው አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመስጠት እየተሰራ ነው” ብለዋል።
አለአግባብ ሀብት ባላቸው ሰዎች የተያዙ የመንግሥት ንግድ ቤቶችን በማስለቀቅ የመስሪያ ቦታ ለሌላቸው ለተደራጁ ወጣቶች ለማስተላለፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተዳደሩ የቀበሌ ቤቶች ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሁለትና ሶስት ቤቶችን የያዙ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ችግሩን በተጠና መልኩ በመፍታት ለችግረኞች ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እስከካሁን በተደረገው ጥረትም በቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን በማሳመን 35 ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶችንና የንግድ ቤቶች መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ በማይለቁ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምት እንደሚወሰድም አብራርተዋል፡፡
የባሌ ዞን የከተሞችና ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም አብዱለቃዲር በዞኑ በሚገኙ ከተሞች የምስተወለውን ህገወጥ የመሬት ወረራን በተደራጀ አግባብ ለመቆጣጠር እየተሰረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በማይገባቸው ሰዎች ተይዘው የነበሩ 120 የቀበሌና የንግድ ቤቶችን ከማስለቀቁም በተጓዳኝ በህገ ወጥ መልኩ የተከናወኑ 700 የጨረቃ ቤቶችን በማፍረስ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል፡፡