የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት መታሰቢያ የእግር ጉዞ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ግንቦት 10/2011 የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመበትን 25 ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የእግር ጉዞ ነገ እሁድ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። 

"እናስታውስ፣ እንተባበር፣ እንታደስ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን የእግር ጉዞ  መርሃ ግብሩን በመተባበር ያዘጋጁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ የሩዋንዳ ኤምባሲ ናቸው።

እንደአውሮፓ አቆጣጠር በ1994 በሩዋንዳ የቱትሲ ጎሳ አባላት ላይ በተፈጸመው የዘር ፍጅት ከ800 ሺህ በላይ ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ተቀጥፏል።

የጭፍጨፋው ሰለባዎችን በማሰብ የወደፊቷ ሩዋንዳና መላው አፍሪካ ከመከፋፈልና ከብጥብጥ በፀዳ የሚገነቡበትን መንገድ ማስገንዘብ የእግር ጉዞው አብይ ዓላማ ነው።

የዘር ጭፍጨፋን አስከፊነት ማስገንዘብ፣ የአንድነትንና እርቅን መንፈስ ማጎልበትም የጉዞው ዓላማ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

መነሻውን ከብሔራዊ ስታዲየም የሚያደርገው የእግር ጉዞው በመስቀል አደባባይ፣ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በብሔራዊቤተ-መንግስት፣ በኢትዮጵያ ሆቴል፣ ብሔራዊ ቲአትር አቋርጦ ብሔራዊ ስታዲየም ላይ ይጠናቀቃል።

በጉዞው ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም