ለአምቦ ከተማ ለ10 ዓመታት የሚቆይ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ማስተር ፕላን ተሰራላት

115

አምቦ ግንቦት 10 / 2011 በምእራብ  ሸዋ ዘን ለአምቦ ከተማ ለ10 ዓመታት  የሚቆይ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ አዲስ ማስተር ፕላን ተሰራላት

አስተዳደሩ በማስተር ፕላኑ ተፈጻሚነት ዙሪያ ከነዋሪዎች ጋር  ተወያይቷል፡፡     

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተረፈ በዳዳ በዚሁ ጊዜ እንዳስረዱት በከተማዋ እየተሰራ ያለው ሶስተኛ መዋቅራዊ የፕላን ክለሳ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮቿን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል።

ከተማዋ ላለፉት 11 ዓመታት በተቀናጀ የከተሞች ፕላን ስትመራ መቆየቷን አስታውሰው፣በአሁኑ ጊዜ ክለሳው በኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲቲዩት ድጋፍ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ፕላኑ ከተማዋንን አገሪቱ የደረሰችበት ደረጃ ግምት ውስጥ ማስገባቱን ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

''ከዚህ በፊት የሚሰሩት ማስተር ፕላኖች ይሰሩ እንጂ፤ ሥራ ላይ በሚውሉበት ጊዜ በተገቢው ሥራ ላይ አልዋሉም ለተፈጻሚነቱም ድጋፍ የሚደርግ የኅብረተሰብ ክፍል አናሳ ነበር''ብለዋል፡፡

ፕላኑ የትምህርት፣  መንገድ፣ አረንጓዴ ልማት፣ የቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቦታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባቱን  አቶ ተረፈ አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ከተሞች ፕላን ኢንስቲቲዩት  ምክትል ዳይሬክተር  አቶ አህመድ ቶፊቅ  ማስተር ፕላኑ  ለስምንት ወራተ ጥናት ሲደረግ እንደቆየ አመልክተው፣በሥራ ላይ እንዲውል ህገ ወጥ የቤቶች ግንባታን በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ተሳታፊዎች  በሰጡት አስተያየት በበኩላቸው ለማስተር ፕላኑ ተፈጻሚነት ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

አምቦ  በፕላን ከሚመሩ የኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ ስትሆን፤በየ10ዓመት የሚከለስ የከተማ ፕላን አሰራር እንደምትከተል ተገልጿል። 

አምቦ ከተማ በ1931 የተቆረቆረች አንጋፋ ከተማ ስትሆን፤ከ104 ሺህ265 ህዝብ ይኖርባታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም