ቀጥታ፡

በሐረሪ ህገወጥ የመሬት ወረራና መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሕብረተሰቡ ጠንክሮ ሊታገል እንደሚገባ ተጠቆመ

ግንቦት  9/2011 በሐረሪ ክልል የሚስተዋሉ ህገወጥ የመሬት ወረራና መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሕብረተሰቡ ጠንክሮ ሊታገል እንደሚገባ የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ ዩሱፍ የክልሉን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በክልሉ ቀደም ሲል ከፀጥታ ጋር በተያያዘ የነበነሩ ችግሮች በአብዛኛው እየተፈቱ በመምጣታቸው በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንጻርዊ ሰላም እየታየ ነው፡፡

ህገወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራ፣ ኮንትሮባንድ ንግድና ህገ-ወጥ የመንገድ ዳር ንግድ በክልሉ በሰፊው እየተስተዋለ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ከህገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ እንዲሁም ህገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድና የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በአቋራጭ ለመበልፀግ በሚሯሯጡ አካላትና ህዝቡን የሚመዘብሩ ደላሎች ላይ የክልሉ መንግስት ተገቢውን እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

“ህገ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ በህጋዊ ነጋዴው ላይ ጫና ከመፍጠር ባለፈ የመንግስት ገቢ እንዳይሰበሰብና የኮንትሮ ባንድ ንግድ እንዲስፋፋ እያደረገ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም የክልሉን ሰላም የበለጠ ለማጠናከር የክልሉ የፖሊስ ኃይል ከፌደራል ፖሊስና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አህመድ፣ ዛሬም ሁከት ለመፍጠር የሚሯሯጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

“የክልሉ የፖሊስ ኃይል ተሀድሶ ከወሰደ በኋላ የነበረበትን ችግር ፈትቶ ለህዝቡ አለኝታ እየሆነና ህዝቡን እየካሰ ነው” ብለዋል። 

እያመጣ ካለው ተጨባጭ ውጤት በመነሳት ህዝቡ ድጋፉን ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው በተለይ ህገወጥ የመሬት ወረራና ተያይዘው የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ትኩረት ሰጥቶ ሊከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ወቅቱ የረመዳን ጾም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰላምና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ የጀመረውን ስለሰላም የመስበክና ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ሊቀጥል” ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከሦስት ቀናት በፊት በከተማው በግለሰቦች ግጭት ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት የአንድ ሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቀ ሀዘን በክልሉ መንግስት ስም የገለጹት አቶ አህመደ፣ ድርጊቱም በህግ ተይዞ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም