ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ስርዓት በትክክል ተግባራዊ አልተደረገም - የዘርፉ ምሁራን

ግንቦት  9/2011  ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓትን በትክክል ተግባራዊ አለማድረጓን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል "ስለ ፌዴራሊዝም እንወያይ" በሚል ርዕስ ከዘርፉ ምሁራን ጋር ውይይት አካሂዷል።

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት ሁለንተናዊ እሳቤዎች ላይ በመወያየት ለስርዓቱ መጎልበት የሚረዳ አማራጭ ሃሳበን ማበርከት ነው።

"ህብረ ብሄራዊነት ምንድን ነው፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሪፎርም ከፌዴራሊዝም አንጻር እንዲሁም ትክክለኛ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር  እንደ መፍትሄ" የሚሉ ሶስት የመወያያ መነሻ ጽሁፎች ቀርበዋል።

በጽሁፎችም በፌዴራሊዝም የሚነሱ የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦች፣ የፌደራሊዝም አተገባባርና ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ሰርዓትን መተግበር ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አስካሁን ያሉ መልካም አጋጣሚዎችንና ተግዳሮቶች ቀርበዋል።

በማዕከሉ የፌዴራሊዝም መምህራን ዶክተር አስናቀ ከፋለ እና ዶክተር ከተማ ወቅጅራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ካላት በርካታ ቋንቋ የሚናገር ሰፊ ህዝብና ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንጻር  የፌዴራሊዝም ስርዓት መከተሏ አግባብ ነው።

ሆኖም በአገሪቷ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፌዴራሊዝም ስርዓት ፍልስፍናው የሚጠይቀውን መመሪያ የተከተለ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ "ትክክለኛ የሆነ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ያስፈልጋታል" ያሉት ዶክተር ከተማ፤ በአገሪቷ እየተተገበረ ያለውን ፌዴራሊዝም "ሐሰተኛ ፌዴራሊዝም" ሲሉ ገልጸውታል።

ክልሎች ነጻ ሆነው ራሳቸውን አለማስተዳደራቸው፣ በክልሎች መካከል የሚኖር የጎንዮሽም ሆነ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የሚደረግ የቀጥታ ግንኙነት በግልጽ መመሪያ አለመተግበሩ እንዲሁም በክልሎች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚመስል መንገድ የፌዴራል መንግስቱን ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው ሽሚያ ለመከራከሪያቸው አስረጂ አድረገው ጠቅሰዋል።

አጠቃላይ ያለው የግንኙነት ሰንሰለት "በፓርቲ ምህዋር እንጂ በህግ አግባብ እየተከናወነ አይደለም" ብለዋል።

የተጠቀሱትን ችግሮች በማስተካካልና የፌዴራሊዝምና ዴሞክራሲያዊ መርሆችን በማጣጣም ትክክለኛ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም መገንባት እንደሚገባ ዶክተር ከተማ ምክረ ሀሳብ አቅብረዋል።

ዜጎች በፌዴራሊዝም ምንነት ላይ የዳበረ ልምድ ስለሌላቸው በየደረጃው የመወያያና የክርክር መድረኮች ሊመቻቹ እንደሚገባም አክለዋል።

አሁን ያለው የፌዴራሊዝም አተገባበር የአንድነትንና የልዩነትን ሚዛን አጣጥሞ እያስተናገደ አለመሆኑን ያሉት ዶክተር አስናቀ ከፋለ ይህ አለመሆኑም "ለአክራሪ ብሄርተኝነት በር ክፍቷል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ህብረ ብሄራዊ አገር እንደመሆኗ በምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ልዩነትና አንድነት የሚስተናገድበት ሁኔታ በግልጽ ሊቀመጥ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ፌደራሊዝምን በትክክል አለመተግበር አደጋው የከፋ እንደሆነም ምሁራኑ በውይይቱ ወቅት አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም