አርማታ ብረት ጭነው ከ20 ቀናት በላይ የቆሙት ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚለቀቁ ተገለጸ

አዳማ ሚያዚያ 22/2010 ከጀቡቲ የአርማታ ብረት ጭነው አዳማ ከተማ ከደረሱ በኋላ በአጨቃጫቂ ሁኔታ ከ20 ቀናት በላይ እንዲቆሙ የተደረጉት 45 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚለቀቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ ። የከባድ ተሽከርካሪዎቹ ሾፌሮች በማያውቁት ምክንያት በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን አዳማ ቅርንጫፍ ሚዛን ተመዝነው መልቀቂያ ለመውሰድ ቢቆሙም ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው ከ20 ቀናት በላይ ለመቆም እንደተገደዱና ለእንግልትና ለኪሳራ እንደተጋለጡ ባለፈው ዓርብ ለኢዜአ መግለፃቸው ይታወሳል ። ሾፌሮቹ የአርማታ ብረቱን ከጅቡቲ መጫናቸው እንጂ ንብረትነቱ የማን እንደሆነ እንደማያውቁም  ተናግረው ነበር ። በኢትዮዽያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት  የጉሙሩክ ስነ ስርዓት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መንግስተአብ ገብረሚካኤል ስለ ሁኔታው ተጠይቀው  " ጉዳዩ እኛን አይመለከትም "  በማለት ወደ ንግድ ሚኒስቴር መጠቆማቸው ይታወሳል ። በንግድ ሚኒስቴር የወጪና የገቢ እቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ እያሱ ስምኦን በበኩላቸው የንብረቱ ባለቤት  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑን ጠቅሰው ለመፈተሽ የብረቱ  ናሙና መቅረብ እንዳለበት መናገራቸው አይዘነጋም ። በወቅቱ የንብረቱ ባለቤት ነው የተባለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥበት  በስልክ ለማነጋገር የተደረገው ጥረት እንዳልተሳካ በዜናው ተገልፆ የነበረ ቢሆንም አሁን  ግን የንብረቱ ባለቤት መፍትሔ ይዞ መቅረቡን ለኢዜአ አስታውቋል ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ነጋሽ ዛሬ እንደገለፁት የአርማታ ብረቱ ወደ ወላይታ የሚጓጓዝና ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ  ጣቢያ ግንባታ አገልግሎት የሚውል ነው። "ተሽከርካሪዎቹ ከ20 ቀናት በላይ መቆም አልነበራቸውም "ያሉት አቶ ምስክር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ስምምነት ላይ በመደረሱ ከዛሬ ጀምሮ እንደሚለቀቁ አስታውቀዋል። ተሽከርካሪዎች በወቅቱ ማስተናገድ ያልተቻለው የጫኑት ብረት ለከፍተኛ ግንባታ የሚውልና ውፍረቱ ከ26 ሚሊ ሜትር በላይ በመሆኑ ጥራቱን ለመፈተሽ የሚያስችል መሳሪያ ባለመኖሩ ነው ብለዋል ። የመፈተሻ መሳሪያው ከሌለ ናሙናው ተወስዶ ብረቱን የጫኑት ተሽከርካሪዎች እንዲለቀቁ መግባባት ላይ በመደረሱ ከዛሬ ጀምሮ መፍትሔ እንደሚያገኙ ተናግረዋል ። ተሽከርካሪዎች አለአግባብ ለቆሙበትና በሾፌሮች ላይ ለደረሰው መጉላላት ተጠያቂው ማን ነው ተብለው የተጠየቁት አቶ ምስክር " በቀጣይነት ብናየው ይሻላል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም