ቀጥታ፡

የአሜሪካን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ተጠየቁ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2011 የአሜሪካን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጠየቁ።

የአሜሪካን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ጠየቁ።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዓለም አቀፍ ትብብር ቢሮ ከሚሊኒየም ቻሌንጅ ኮርፖሬሽን ጋር በመሆን "የኢትዮጵያ አጋርነት ጉባኤ" በአሜሪካ ዋሺንግተን አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካው አምባሳደር ማይክል ራይነር በዚሁ ጊዜ አንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በፖለቲካውና በምጣኔ ኃብት ዘርፍ የተሰራው ሥራ ለኢንቨስትመንት ሥራው አመቺ ነው።

የኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ሞዴል ከመንግሥት መሪነት ወደ ግል መዘዋወሩ በራሱ ለግል ባለኃብቱና ለኢንቨስትመንት ትልቅ እድል ይፈጥራል።  

ይህም በአገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲን መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማዳበር በሚደረገው አገራዊ የለውጥ ማዕቀፍ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የአገራቸው ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ በስፋት አንዲሰማሩና ኢትዮጵያ ጠንካራና ያደገ ምጣኔ ኃብት አንዲኖራት የበኩላቸውን አንዲወጡ ጠይቀዋል።

በጉባኤው ላይ ከ400 በላይ ከአሜሪካና ከኢትዮጵያ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት እንዲሁም ባለኃብቶች ተሳትፈዋል።

በጉባኤው የፋይናንሰ አቅርቦት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦትና ዘመናዊ ግብርን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል።   

የአሜሪካው የንግድ ማኅበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ 41 የአሜሪካ ባለኃብቶች የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ እንዲሰመሩ አድርጓል።

ይህም ጉባኤ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ኢንቨስትመንት ትብብር ለማቀላጠፍ ያለመ መሆኑን የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም