የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ
ግንቦት 9/2011 የትምህርት ዘመኑ ሊጠናቀቅ የቀረው አጭር ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎች ወደ መደበኛ ትምህርታቸው ፈጥነው እንዲመለሱ የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጥሪ አቀረበ ።
በተቋሙ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት መስተጋጎልን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎች ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ትምህርት ማቋረጣቸውን ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ ሞላ ለኢዜአ እንደገለፁት በተቋሙ ውሀ መስመር ላይ በደረሰ ብልሽት አገልግሎቱ ተቋርጦ ነበር።
ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ ውሃ ባለመቅረቡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን ተናግረዋል ።
"የውሃ አቅርቦት ችግሩ ቢፈታም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል" ብለዋል ።
የኃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ተማሪዎቹን እንዲያነጋግሩ ጥረት መደረጉን ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል።
የውሃ አቅርቦት ችግሩ ስለተፈታና የትምህርት ዘመኑ ሊጠናቀቅ የቀረው አጭር ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎች ፈጥነው መደበኛ ትምርታቸውን እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል
ዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰባሳቢ አቶ ትንሣኤ መኮንን በበኩላቸው የችግሩ መንስኤ የውሀ መስመር በመበላሸቱ አገልግሎቱን በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአምስት ቀናት ውሀ በቦቴ በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
"ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓም ከጧት ኤሌክትሪክ በመቋረጡ ውሀን በቦቴ ማቀረብ ባለመቻሉ ተማሪዎች በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል" ብለዋል፡፡
የተስተጓጎለው የውሀ አቅርቦት ችግር በመፈታቱ የትምህርት ዘመኑ ሊጠናቀቅ አጭር ጊዜ የቀረው በመሆኑ ተማሪዎች ያቋረጡትን ፈጥነው እንዲጀምሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።