ቀጥታ፡

የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ ማህበሩን አይወክልም - የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር

ግንቦት 8/2011 የህክምና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ የማንደግፈውና ማህበሩን የማይወክል ነው ሲል የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ገለጸ።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንደምናቀርብ ቢገለጽልንም በውይይቱ ላይ ያዘጋጀናቸውን ጥያቄዎች ለማቅረብ እድል አልትሰጠንም ብሏል ማህበሩ።

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ገመቺስ ማሞ ማህበሩ ላለፉት 10 ዓመታት በጤና ዘርፍ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ሲሟገትና ትግል ሲያደርግ ነበር ብለዋል።

የጤና አገልግሎት ጥራት፣ የጤና ተቋማት ተደራሽነት፣ ብቁ የሆነ የጤና ባለሙያ ማፍራት፣ የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ ጥራት ያለው የህክምና ትምህርት እና የመድሐኒት አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች ማህበሩ ከዚህ በፊትም ሲያነሳቸው የነበሩ ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

በህክምና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢና ወቅታዊ እንደሆኑ ገልጸው ጥያቄዎቹ ወሳኝ እና በዝርዝር ታይተው መፍትሔ ሊሰጥባቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ጥያቄዎቹን ማቅረብ ተገቢ ሆኖ ሳለ በህክምና ባለሙያዎች በኩል እየተደረገ ያለው የስራ ማቆም አድማ ማህበሩ በፍጹም የማይደግፈውና የህክምና ማህበሩን እንደማይወክልም ተናግረዋል።

ከሌሎች የህክምና ማህበራት እና ኢኒሼቲቮች ጋር ባደረግነው ውይይት ጥያቄውን ማቅረብ ተገቢ እንደሆነና የስራ ማቆም አድማ ማድረግ አግባብነት የሌለው መሆኑን እንደገለጹላቸው አስታውቀዋል።

የህክምና ባለሙያ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ ከምንም በላይ ህብረተሰቡን አደጋ ላይ የሚጥልና ሙያውንም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳ ተግባር እንደሆነ ነው ዶክተር ገመቺስ ያስረዱት።

"በጤናው ዘርፍ ያሉ ጥያቄዎች ቢኖሩ እስከ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት ድረስ ማህበሩ እንደሚሄድ ገልጸው የስራ ማቆም አድማ ማድረግ የማናልፈው ከባድ ቀይ መስመር ነው" ብለዋል የማህበሩ ሊቀመንበር።

ማህበሩ ሚያዚያ 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጤና ባለሙያዎች ያደረጉትን ውይይት በበጎ ጎኑ እንደሚያየውና በጤና ዘርፍ ያለውን ችግር  ለመፍታት ያለውን ተነሳሽነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ያም ቢሆን የህክምና ማህበሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ጥያቄ የማቅረብ እድል ከውይይቱ በፊት እንደምናገኝ የተገለጸልን ቢሆንም ማህበሩ ማንሳት የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች ለማቅረብ እድል እንዳላገኘ ገልጸዋል።

ጥያቄ የማቅረብ እድሉን ባለማግኘቱ ቅር ብንሰኝም ከሞላ ጎደል ጥያቄዎቹ በጤና ባሙያዎቹ መነሳታቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ምክትል ሊቀ-መንበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን በመግለጫው ወቅት አንስተዋል።

የጤና ፖሊሲ ማሻሻያ፣ የጤና ዘርፍ በጀት በቂ አለመሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ብቻውን ብዙ ሃላፊነቶችን ደርቦ መያዙ አግባብ አለመሆኑ፣ የፌዴራል ሆስፒታሎች በራሳቸው የአስተዳደር ስርአት ቢተዳደሩ፣ የህክምና ባለሙያዎች እስርን ጨምሮ ያለ አግባብ የሚደርስባቸው አካላዊና ሞራላዊ ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

የሚታመሙ ይህክምና ባለሙያዎች በሌላ የህክምና ተቋም የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣የጤና ባለሙያዎች ደመውጨወዝ መጨመር የትርፍ ሰአት ክፍያ በአግባቡ እንዲፈጸም፣ መኖሪያ ቤት እንዲሰጥ፣ በጤናው ዘርፍ ያሉ ችግሮች በዘላቂነት የሚፈታ የአሰራር ስርአት መዘርጋት የሚሉት የማህበሩ ጥያቄዎች ናቸው ብለዋል ዶክተር ብርሃኑ።

ጥያቄዎቹ በዝርዝር ታይተው መፍትሔ እንዲሰጥባቸውና መንግስት የደረሰበትን ደረጃ ለህክምና ባለሙያዎችና ለህዝብ ማቅረብ እንደሚገባው ተናግረዋል።

መንግስት በጤና ባለሙያዎቹ የተነሱትን ጥያቄዎችን ለምስጠት ያለው ተነሳሽነት ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ገልጸው የህክምና ባለሙያዎች እያነሱት ያለው ጥያቄ ተገቢነት ያለው መሆኑን ህብረተሰቡ ሊያውቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ማህበሩ የስራ ማቆም አድማውን በተመለከተ የስራ ማቆም አድማውን ማን እንደጠራ የሚያውቀውን ነገር እንደሌለ እና ማህበሩ በስራ ማቆም አድማ ዙሪያ የደረሰው ምንም አይነት ደብዳቤ የለም ብለዋል።

የስራ ማቆም አድማ የተመለከቱ መረጃዎች የሚለቀቁት በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እንደሆነና የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በጤና ባለሙያዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በማህበራዊ ሚዲያው እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች የማህበሩ አቋም እንዳልሆኑ የትኛውም አካል ማወቅ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር በ1954 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን አራት ሺህ የሚሆኑ አባላት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም